በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን መከላከል የሁሉም አካል ሃላፊነት ቢሆንም የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ተቋም የህጻናትን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የወጡ ህጎች፣ ደንቦች፣አሰራሮች ስምምነቶች ወዘተ. ተግባራዊ እንዲሆኑ በበላይነት ያስተባብራል፡፡ አፈጻጸማቸውን ይከታተላል፡፡
በሴቶችና ህጻናት ላይ ጥቃቶችና የመብት ጥሰቶች ሲፈጸሙም ተጠቂዎች ተገቢውን የህክምና እና የስነልቦና እንዲሁም ሌሎች ድጋፎችን እንዲያገኙ ጥቃት አድራሾችም ተገቢና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው/አስተማሪ ቅጣት እዲያገኙ/ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በሀገራችን ኢትዮጽያም ሆነ በክልላችን ልንከባከባቸው፣ ልናጐለብታቸውና ከትውልድ ትውልድ ልናስቀጥላቸው የሚገባቸው በርካታ ጠቃሚ ባህሎች፣ወጎች ልምዶች ያሉትን ያክል በርካታ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡
እነዚህ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች በአብዛኛው በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ ሲሆኑ በተጎጅዎች ላይ የሚያደርሷቸው የጤና፣ የአካል፣ የሥነ ልቦናና ማህበራዊ ተፅዕኖዎች ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የሃገሪቱንም ሆነ የክልሉን ሁለንተናዊ የዕድገት እንቅስቃሴ ወደ ኋላ የሚጐትቱ ናቸው፡፡
ስለሆነም ይህንን ችግር መቀነስ ብሎም ማጥፋት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሰውን ማህበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ለመቀነስ አልፎም የክልላችን ሁለንተናዊ የዕድገት እንቅስቃሴ ለማፋጠን አንዱ እና ዋነኛዉ መሳሪያ በመሆኑ ድርጊቶችን በተደራጀ እንቅስቃሴ ለመግታት ይቻል ዘንድ ከክልል እስከ ቀበሌ የጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ጥምረት ተቋቁሞ ድርጊቱን ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም እየተሰራ ይገኛል፡፡
የአብክመ ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የክልሉ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ጥምረት የቴክኒክና የስትሪግ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ጥምረት የ2016 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017 እቅድ ትውውቅ እና የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማእከላት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረገ የምክክር መድረክ መስከረም 8/ 2016 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ አካሄዷል፡፡
በእለቱ ተገኝተው የእንኳን ደህና ጣችሁ መልእክት አስተላልፈው ፕሮግራሙን የከፈቱት የቢሮው ምክ/ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዝና ጌታቸው በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ አይነታቸውን እና ስልታቸውን እየቀያየሩ እጅግ ከሰባዊነት በራቀ ፣ ከባህላችን ፣ ከእሴታችን ባፈነገጠ አግባብ እየተፈጸሙ መሆኑን ጠቁመው
በክልላችን የተቋቋመው የጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ጥምረት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራቱን ጨምሮ ጥቃቶች ሲደርሱ የሀይል የጥቃት ሰለባ ለሆኑ ሴቶች እና ህጻናት የህክምና፣ የስነልቦና፣ የፍትህ ፣ የምግብና የመጠለያ አገልግሎት በተቀናጀ እና ሁሉን አቀፍ አገልግሎት የሚሰጥበት የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት አሁናዊ ሁኔታን በአግባቡ በመዳሰስ በቀጣይ በተለይ ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ወቅቱን የሚመጥን ስራ በመስራት የሴቶችና የህጻናትን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ አለብን፡፡ ብለዋል፡፡
በምክክር መድረኩም ከፍትህ ቢሮ የሰባዊ መብት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ እሸቱ አለነ እና በክልላችን ያሉ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር ያሉበት አሁናዊ ሁኔታ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ እና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት በአቶ አስናቀ ለወይ እንዲሁም የጎጅ ልማዳዊ ድርጊት አስወጋጅ ጥምረት የ2016 በጀት አመት እቅድ አፈጻጸም እና የ2017 እቅድ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ እና ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት በወ/ሮ ደስታ ፈንታ አማካኝነት በዝርዝር ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የውይይት ተሳታፊዎቹ ከፍትህ፣ ከጤና ፣ከፍርድ ቤት፣ ከፖሊስ፣ ከኮሙኒኬሽን ከእምነት ተቋማት እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ አመራሮችና ባለሞያዎች ሲሆኑ በውይይቱ የወልና የተናጠል ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ከመወጣት ፣ በየማእከላቱ እየተከናወኑ ያሉ አበይት ተግባራት ካጋጠሙ ችግሮችና ከተወሰዱ መፍትሄዎች እንዲሁም ከግንዛቤ ፈጠራና ስራና በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ያሉ የተሻሉ ተሞክሮዎችን ለማምጣት የልምድ ልውውጥ ከማድረግ ጋር የተያያዙ ጥያቄ ሃሳብ አስተያየት ተሳታፊዎች በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
ውይይቱን የመሩት በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክ/ ኃላፊ ወ/ሮ ዝና ጌታቸው እና የፍትህ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊአቶ ወንዳቸው ሲሆኑ በተነሱ ጥያቄዎችና ሀሳብ አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጫ ማዕከል ላይ የሚያገለግሉ ባለሙያዎች ተደጋጋሚ የሆነ የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት፣ የጥምረቱ አባል ተቋማት አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ተገቢውን ትኩረት መስጠት ተግባርና ሃላፊነቶችን በአግባቡ መወጣት ፣ ለማእከሎች አስፈላጊ ግብዓት ሟሟላት፣ ጠንካራ የድጋፍና ክትትል ስርዓት መዘርጋት፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እና አሉ የተባሉ ችግሮችን መፍታት በቀጣይ በልዩ ትኩረት በመስጠት የሚሰሩባቸው ነጥቦች እንደሆኑ አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም አካል በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸም ማንኛውንም ጥቃት በጋራ እንዲከላከል ጥቃት፡ ተፈጽሞ ሲገኝም ተጠቂዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ፣ ጥቃት ፈጻሚዎች ደግሞ በህግ እንዲጠየቁ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በማድረግ ከተበዳዮች ጎን እንዲሰለፉ በቅንጅት እንደሚሰሩ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ውይይቱ ተጠናቋል ፡፡



