የአፍሪካ ወጣቶች ቀን በአፍሪካ ለ19ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ “የዳበረ የወጣቶች ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ መልዕክት ከጥቅምት 21 እስከ ኅዳር 21/2018 ዓ.ም እየተከበረ ነው።
የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዘላለም አረጋ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክትል ኀላፊው እንደገለጹት የአፍሪካ ወጣቶች ቀን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እየተከበረ ነው ብለዋል።
የዚህ በዓል መከበር አላማ ወጣቶቹን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኹነቶች ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ለመዘከር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይም በሀገሪቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ የመፍትሔ ሀሳብ እንዲያመነጩ ሁሉንም ወጣቶች ማሳተፍ ይገባልም ብለዋል።
እምቅ አቅም ያላቸውን ወጣቶች በሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ማበረታታት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በሀገሪቱ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና ፕሮግራሞች ዙሪያ የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ባለቤት እንዲኾኑ ማስቻል ይኖርብናል ብለዋል።
የወጣቶች ቀን መከበርም ወጣቶች ወጋቸውን፣ ባሕላቸውን እና የሥራ ተነሳሸነታቸውን እንዲያጠነክሩ ለማድረግ አይነተኛ መሳሪያ ነው ብለዋል።
በበዓሉ ላይ በየደረጃው የሚገኙ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ተሳታፊ ይኾናሉ ብለዋል።
የዚህ መድረክ መዘጋጀት በወጣቶችና አጋር አካላት ላይ ጠንካራ ቅንጂታዊ አሠራር ይፈጥራል ብለዋል።
አሚኮ

