ተቋማት የሴቶችን፣ የህጻናትን፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካተው በመስራት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ከመቸውም ጊዜ በላይ በልዩ ትኩረት እንሰራለን፡፡/የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ/

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ ፣ በሁሉም መስክ የሚኖራቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲያድግ ፣የወጡ የህግ ማእቀፎች፣ስምምነቶች ተግባረዊ እንዲሆኑ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መካከል ተቋማት የሴቶችን፣ የህጻናትን፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካተው እንዲሰሩ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እገዛ፣ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ቁጥጥር ማድረግ በመሆኑ ይህንን ተግባር ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በተሻለ ለመፈጸም ከተቋማት አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በመፍጠር፣ተግባሩን ለማሳለጥና ሁሉም ተቋማት ወጥ በሆነ መልኩ ዘላቂነት ያለው ተግባር እንዲፈጽሙ የሚያስችል ሰነዶችን በማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ሰሞኑንም ከክልል የመንግስት ቢሮዎች ለተውጣጡ ዳይሬክተሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በአዲሱ የተቋማት አካቶ ትግበራ መመዘኛ ማዕቀፍ ላይ ለ3 ተከታታይ ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ስልጠናው በሴቶች፤ህፃናት፤አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጉዳይ ማካተትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ሰለሞን ክንዱ እና በሌሎች የዳይሬክቶሬቱ ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ስልጠናው በቡድን ውይይትና በተግባራዊ ሙከራ የታገዘ ነበር፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው የቀጣይ የስራ አቅጣጫ የሰጡት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ በመፈጸም የተቋሙ ደንበኞች በሁሉም መስክ የሚኖራቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲያድግ መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የተቋማት እገዛ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ቢሮ ኃላፊዋ አያይዘውም ቢሮው ግንዛቤ ከመፍጠር፣ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ ተቋማት በአካቶ ትግበራ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ምዘና ማድረግ እንደተጀመረ እና እስከ አሁንም ወደ 15 ቢሮዎች በአዲሱ የመመዘኛ ማእቀፍ አማካኝነት መመዘናቸውን ገልጸው

የስልጠናው ዋና አላማም ምዘናው በዙር የሚካሄዱ በመሆኑ በቀጣይ ለሚመዘኑ ተቋማት ሃላፊዎች የምዘና ማዕቀፍን በማስተዋወቅና አጠቃላይ በአካቶ ትግበራ ላይ ውይይት በማድረግ ምዘናውን በእውቀት ላይ ተመስርተው በውጤታማነት እንዲያከናዉኑ አልፎም ለአካቶ ትግበራው ውጤታማነት በልዩ ትኩረት እንዲሰራ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ ይህን አላማ ለማሳካትም ከምንጊዜውም በላይ ከተቋማት ጋር በጠንካራ ቅንጅት እንደሚሰሩ እና ለሌሎች ቀሪ ተቋማትም ተመሳሳይ መድረክ በቀጣይ እንደሚካሄድ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎች ተቋሙ ተቋማት ለአካቶ ትግበራ የሚሰጡት ትኩረት እንዲያድግ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበው ተቋማቸውን በመመዘን በምዘናው ውጤት መሰረት ችግራቸውን በመለየት የማስተካከያ እርምት ለመውሰድ የሚያስችላቸው እውቀትና ክህሎት እንዳገኙ እና ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሚመደብላቸው ባለሙያ ጋር በመተባበር እስከ ጥቅምት ወር አጋማሽ ድረስ ተቋማቸውን መዝነው እንደሚያሳዉቁ መግባባት ላይ በመድረስ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡

መስከረም 21 /2017 ዓ.ም

ባህር ዳር ከተማ

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top