የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም ገምግሟል። በግምገማዊ ውይይቱ የዞን መምሪያ ኀላፊዎች የሴቶች አደረጃጀቶች እና የአረጋውያን ፌዴሬሽን መሪዎች ተሳትፈዋል።
በግምገማው መክፈቻ መልዕክት ያስተላለፉት የቢሮው ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በሩብ ዓመቱ በሴቶች ልማት ኅብረት አደረጃጀት፣ በጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ በሴቶች የምጣኔ ሃብት እና የትምህርት ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል።
በወቅታዊ የሰላም ችግር ምክንያት ሕጻናት ላይ የሚደርስ ችግርን ለመቀነስ የሚሠሩ ሥራዎች እና ያጋጠሙ ችግሮችን ለማለፍ እንዲሁም በሕጻናት ማቆያ አተገባበር ላይ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
አረጋውያን በራሳቸው አደረጃጀት እንዲጠቀሙ ሕንጻ የመገንባት ሥራው ምን ደረጃ እንዳለ፣ መሥራት የሚችሉትም እንዲሠሩ፣ አካል ጉዳተኞች በችሎታቸው ሠርተው እንዲኖሩ በማድረግ በኩል ያሉ ክፍተቶችን አርሞ የመሥራትን አስፈላጊነት አንስተዋል።
አካል ጉዳተኞችን ትምህርት ለማስጀመር በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልግ እና ሥልጠና አግኝተው ሥራ እንዲፈጥሩ ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ መፍታት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ተረጅነትን ከመቀነስ አኳያ የተረጅዎችን መረጃ መያዝ እንደሚያስፈልግ ያነሱት ቢሮ ኀላፊዋ ሁልጊዜ መርዳት ብቻም ሳይኾን መሥራት የሚችሉትን መለየት እና ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደገፍ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
የገጠር ሴፍቲኔት አገልግሎትን ማኅበራዊ ትስስር የማስፋትን አስፈላጊነትም አንስተዋል። የአካቶ ትግበራንም ትኩረት ሰጥቶ ተቋማትን መከታተል እና መመዘን እንደሚገባም ገልጸዋል።
የቢሮው የዕቅድ እና በጀት፣ ክትትል እና ግምገማ ዳይሬክተር ብርሃኑ አለሙ በበጀት ዓመቱ 1ኛ ሩብ ዓመት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በማሠባሠብ ሴቶችን በሥራ በማሳተፍ የገቢ ማስገኛ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎትም የአረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችን ቤት ሥራ እና ጥገና ተከናውኗል ብለዋል።
በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ጾታዊ እና የሥነ ልቦና ጥቃት መግጠሙንም ገልጸዋል። የችግሩ ሁኔታ እየተጠና መኾኑን እና ከባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ጦይባ አሕመድ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰው ነገር ግን በቅንጅት መሥራት ላይ ቀሪ ሥራዎች ሥለመኖራቸው ገልጸዋል።
ሕጻናትን በትምህርት ሥርዓቱ እና በጤናው ከመገንባት አኳያ መሠራት ያለበት ሥራ መኖሩንም ጠቅሰዋል። ለዚህም የግንዛቤ ፈጠራ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ናርዶስ ቢራራ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን ተጠቃሚ ለማድረግ ከጥቃቶች መከላከል እና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ሁሉም በጋራ መሥራት እንዳለበት ነው የገለጹት። በክልሉ ያለው ግጭትም የበለጠ ተጎጅ ስለሚያደርጋቸው ሰላምን ማስፈን ዘለቄታዊ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።



