”ለአረጋውያን የሚደረገው ድጋፍ ለሀገራዊ አበርክቷቸው እውቅና መስጠት እንጂ ልዩ ችሮታ አይደለም” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋውያን ቀንን አከባበር ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት አከናውኗል።

”ክብር እና ፍቅር ለአረጋውያን” በሚል መሪ ቃል ለ33ኛ ጊዜ ሲከበር በሰነበተው የዓል ማጠቃለያ መርሐ ግብር በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኘው ዝግባ የሕጻናት እና የአረጋውያን መርጃ የበጎ አድራጎት ድርጅት አረጋውያን ማዕድ አጋርቷል። የብርድ ልብስ እና አንሶላ ድጋፍም ተደርጓል።

ሥነ ሥርዓቱ ቀጥሎም የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ፣ የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮች፣ የዞን መምሪያ ኀላፊዎች፣ የአረጋውያን ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተከናውነዋል።

በአረጋውያን ድጋፍ ዙሪያም ጽሑፍ ቀርቧል። አረጋውያንን በማገዝ የበለጠ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ተቋማት፣ ግለሰቦች እና በጎ አድራጊ ድርጅቶች ተመስግነዋል። በዘርፉ ሥራዎች የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ዞኖችም ተሸልመዋል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ

አረጋውያን ለሀገራቸው ያገለገሉ እና ዛሬ ደግሞ ሰፊ ልምዳቸውን የሚያበረክቱ ዜጎች ናቸው ብለዋል።

በትናንት ሀገር ግንባታ ያገለገሉ አረጋውያን ድርሻቸው ትልቅ እንደኾነም ጠቅሰዋል። ስለዚህ እነሱን መጦር ማለት ለከፈሉት አስተዋጽኦ እውቅና መስጠት መኾኑን ገልጸዋል።

የሀገራችን የረጂም ዓመት ታሪክ በዛሬዎቹ አረጋውያን ያለመታከት የተሠራ እና ለዛሬው ትውልድ የተበረከተ ነው። ትውልዱ አርእያቸውን በመከተል ሀገርን ከማስቀጠል ሌላ ውለታቸውን ከፍሎ አይጨርሰውም ብለዋል።

ዛሬም የሀገራችንን ጠቃሚ እሴቶች አቆይቶ በማስተላለፍ ያላቸው ድርሻ ትልቅ ነው። ተከባብሮ እና ተዋድዶ መኖር ከአረጋውያን የምንማረው ትልቅ እሴት ነው። ጥበባቸውንም ትውልዱ ሊማር ይገባል ነው ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ።

አረጋውያን ለዛሬው ትውልድ ለማስተላለፍ ትላንት ሳይሰለቹ የደከሙባትን ሀገር ዛሬም አቅማቸው በፈቀደ ልክ አብሮ የመኖር እና የመተሳሰብ እሴትን እንዲያስተላልፉ አፈ ጉባኤዋ አደራ ብለዋል።

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችንም በሰው ተኮር የመንግሥት ሥራዎች እና አጋር አካላት በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

”ለአረጋውያን የሚደረገው ድጋፍ ላደረጉልን ነገር እውቅና መስጠት እንጂ ልዩ ስጦታ አይደለም” ያሉት ዋና አፈ ጉባኤዋ ማኅበራቶቻቸውን በማጠናከር የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። አረጋውያንን መንከባከብ ውዴታ ብቻ ሳይኾን ለሀገራችን የምንሰጠው ግዴታም ነው ሲሉ አክለዋል።

የአረጋውያንን ቀንን በአንድ ሰሞን ብቻ ተከብሮ የሚጠናቀቅ መኾን እንደሌለበት ያሳሰቡት አፈ ጉባኤዋ በቀጣይም ዓመቱን በሙሉ የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረገ ሥራዎች እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top