ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን በባህር ዳር ከተማ በልዩልዩ ሁነቶች ተከብሮ ውሏል፡፡
ባህር ዳር፡ ጥምቅምት 11/2017 ዓ.ም (አማራ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ)በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን በሃገራችን ለ33ኛ ጊዜ ”ክብርና ፍቅር ለአረጋውያን” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው አለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ በዓል የክልል ተቋማት ኃላፊዎች የዞን ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ሃላፊዎች በአረጋውያን ዙሪያ የተሰማሩ አጋር አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በባህር ዳር ከተማ በልዩ ልዩ መርሃ ግብሮች ተከብሮ ውሏል፡፡
በፕሮግራሙ በዝግባ የአረጋውያንእና ህፃናት መርጃ ማዕከል ለሚገኙ አረጋውያን እና ህፃናት የአልባሳት እርዳታ እና የማዕድ ማጋራት ስነስርዓት የተከናወነ ሲሆን በእለቱ የነበሩ ተጋባዥ እንግዶች ማዕከሉን ጎብኝተዋል ፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በክልሉ ለ1ሺህ 750 አረጋውያን ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልፀው ዝግባ እና ሌሎች የአረጋውያን እና የህጻናት መርጃ ማዕከላት ለአረጋዊያንና ህጻናት እያደረጉት ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ያብራሩት ኃላፊዋ ድጋፍ የሚሹ አረጋዊያንን ከአጋር አካላት ሃብት በማሰባሰብ ብቻ ልናኖራቸው ስለማንችል በዘላቂነት የሚረዱበትን መንገድ ክልሉ እያመቻቸ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም አረጋውያን በተለያዩ የስራ ዘርፎች በመሰማራት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት ገቢ የሚያገኙበት መንገድ እየተመቻቸ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ብርቱካን መስራት ለማይችሉ አረጋውያን ከመንግስት ቦታ በመቀበል የተለያዩ ህንፃዎችን ሰርቶ በማከራየት ገቢ የማግኛ ዘዴ እየፈጠርን ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም በአሁን ሰዓት በምስራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ ፣በሰሜን ሸዋ አረርቲ ወረዳ ፣በምእራብ ጎንደር ሳንጃ ወረዳ ተጀምረው በቅርቡ የሚጠናቀቁ ህንጻዎች መኖራቸውን እና በደቡብ ወሎ ፣ዋግ ኸምራ እና በወልድያ ከተማ የተጀመሩ ስራዎች እንዳሉ አብራተዋል፡፡
ምንጭ፡- አማራ ኮምንኬሽን


