ባሕር ዳር: ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገራችን ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ሥራ መጠቀም ብዙም አልተለመደም፡፡ እንዲያውም የማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ማንነትን ደብቆ ለመጥፎ ዓላማ ማዋል የተለመደ ነው፡፡ በሀገራችን ለሰላም እጦት እና ለዜጎች ደኅንነት ሥጋት ከሚፈጥሩት መካከል ውስጥ አንዱ እና ዋናው ማኅበራዊ ሚዲያችን የሚሉ አሉ፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ባይበዙም ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ ዓላማ የሚጠቀሙ ዜጎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ሞሐመድ አል አሩሲ፣ ኡስታዝ ጀማል በሽር፣ መልዕክተኛው እና የመሳሰሉት ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ለሀገር፣ ለሕዝብ እና ለችግረኛ ወገኖች ጠቃሚ ሥራ በመሥራት የሚበረታቱ ጅምሮች አሉ፡፡ ይህም ቴክኖሎጂን ለበጎ ዓላማ የመጠቀም ተስፋን ያመላክታል፡፡
በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ የኾነው ወጣት አግማሴ ዋጋው ለዚህ ሃሳባችን አብነት ነው። ወጣቱ ፌስ ቡክ፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብን በመጠቀም ችግረኞችን ይረዳል፡፡ ሥራውን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እንደጀመረ የሚናገረው አግማስ አሁን ላይ በሰፊው እየሠራበት እንደኾነም ገልጿል፡፡ ለዚህ በጎ ሥራውም የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እውቅና እና ምስጋና ችሮታል፡፡
ሕይዎቱን የሚመራው በንግድ ነው። በቀሪ ጊዜው የተቸገሩ፣ የማኅበረሰብ ድጋፍ የሚስፈልጋቸውን እና በማኅበረሰብ ተሳትፎ ሊሰሩ የሚገባቸው የልማት ሥራዎችን በማኅበራዊ መረጃ በማድረስ፣ በመቀስቀስ እና በማሳመን ይሠራል፡፡ ቃል የተገቡ እና የተገኙ ድጋፎችንም በማሠባሠብ ለችግረኞች ያደርሳል፡፡
ረዳት የሌላቸው ችግረኞችን ወደ ሚዲያው በማውጣት ማኅበረሰቡ እንዲያግዛቸው ያደርጋል፤ ራሱም ያግዛል።
ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖችን ችግር፣ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ዓይነት እና አድራሻቸውን በመግለጽ ኅብረተሰቡ እንዲደግፋቸው እንደሚያደርግ ነው የተናገረው፡፡ እስካሁን 20 ሰዎችን በቋሚነት እና አምስት ሰዎችን ደግሞ መቋቋሚያ ተሰጥቷቸው ሥራ እንዲጀምሩ በማድረግ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ሌሎቹ ወቅታዊ ችግሮችን የመቅረፍ ወይም የማስታገስ ድጋፍን እንደሚያስተባብርም ነግሮናል፡፡
በዋናነት በደብረ ታቦር እና አካባቢው ቢሠራም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ፣ በወሎ እና በባሕር ዳር ከተማ ከዕለት ድጋፍ እስከ ሕክምና ድረስ አሥተባብሮ ችግረኞችን ደግፏል።
የማኅበራዊ ሚዲያን ጠቀሜታ በመረዳት ተባብሮ መሥራት ቢቻል ኅብረተሰቡን የበለጠ ማገልገል እንደሚቻል ያነሳው ወጣቱ ማኅበረሰቡ ስለ ማኅበራዊ ሚዲያ ያለውን ግንዛቤ ለማስተካከል አስተምራለሁ ብሏል።
ከሌሎች ጋር ተረዳድቶ መሥራት ጀምሯል። መልዕክተኛው በሚል ሥም ከሚታወቅ በጎ አድራጊ ወጣት ጋርም በመረዳዳት እንደሚሠራ ገልጿል፡፡
ሰዎች ችግራቸው ተቀርፎላቸው ሲደሰቱ ማየት እንደሚያስደስት የጠቀሰው ወጣት አግማሴ በቀን ቢያንስ አንድ ችግረኛ ሰው እንደሚጠይቅ ነግሮናል።
ማኅበራዊ ሚዲያን ለበጎ በመጠቀም ሽፋን ላልተገባ የግል ጥቅማቸው የሚያውሉም አይጠፉምና ምን አስተያየት አለህ በሚል ለቀረበለት ሃሳብም በችግረኞች ሥም የተሠበሠበን ገንዘብ ለዓላማው መዋሉን በሚያረጋግጥ መልኩ እንደሚያደርስ ነው የገለጸው። እውነተኛ እና ሐሰተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ለይቶ ማወቅ እና የሰጡት ድጋፍ ለተባለለት ዓላማ መዋሉን መከታተል እንደሚያስፈልግ መክሯል።
ለችግረኞች የተለያዩ ድጋፍ በተለያዩ ጊዜያት ስለሚያደርግ መጠኑን ባያውቀውም የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአረጋውያንን ቀን ሲያከብር ባደረገለት ሽልማት የ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዳደረገ ተገልጿል። ወጣት አግማስ በበኩሉ በምሥራቅ ጎጃም ሞጣ፣ በወሎ እና በባሕር ዳር ከመሰል ጓደኞቹ ጋር በድጋፍ የሠራው ሲጨመር እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ይጠቅሳል።
ማኅበራዊ ሚዲያን በሰፊው በመጠቀም ሰዎችን መርዳት እንደሚቀጥል የገለጸው አግማስ ሥራውን በጥራት፣ በፍጥነት እና በውጤታማነት ለመሥራት የመሥሪያ ቁሳቁሶች እንደሚፈልግ ገልጿል።
ፎቶ፣ ቪዲዮ እና ድምጽ መቅረጫ እንዲሁም የማቀናበሪያ ኮምፒዩተር ቢያገኝ ሥራውን የበለጠ እንደሚያቀላጥፍለት ተናግሯል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
ምንጭ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን

