የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ አለም አቀፍ የታዳጊ ልጃገረዶች ቀንን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የበዓሉ ዋነኛ ባለቤት የሆናችሁ ልጃገረዶች በተገኙበት “ታዳጊ ሴቶች ላይ መሥራት የነገን የተሻለ ሀገር መገንባት ነው” በሚል መሪ መልዕክት በፓናል ውይይት አከበረ፡፡

ዓለም አቀፍ የታዳጊ ሴቶች ቀን እኤአ ታህሳስ 19 ቀን 2011 በተደረገ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ በፈረንጆች ጥቅምት 11 ቀን የታዳጊ ሴቶችን መብት የሚከበርበት ቀን እንዲሆን ካወጀበት ጊዜ ጀምሮ በየአመቱ በፈረንጆ ጥቅምት 11 የተለያዩ መሪ ቃሎችን በማነገብ የታዳጊ ሴቶችን ተሳትፎ የሚረጋገጥበት፣መልክቶቻቸውን የሚያስተላልፉበት፣ ጥያቄዎቻቸውን በሚያቀርቡበት አግባብ እና እርስ በእርሳቸው የፓናል ውይይቶችን በሚያካሄዱበት ሁኔታ ሲከበር የቆየ ሲሆን የዘንድሮ አለም አቀፍ የታዳጊ ልጃገረዶች ቀንም በአለም አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ “Girls’ Vision for the Future,” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ደግሞ ለ13ኛ“ጊዜ ታዳጊ ሴቶች ላይ መስራት የነገን የተሻለች ሀገር መገንባት ነው” በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል ጥቅምት 1 ቀን የተከበረ ሲሆን በክልላችን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በዛሬው እለት የተከበረው፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኀበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እንዳሉት የልጃገረዶችን ዓላማ እና ራዕይ ግምት ውስጥ አስገብቶ ቀኑን ማክበር ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ አያይዘውም “ልጃገረዶች ለሀገር እና ወገን ጠቃሚ እንዲኾኑ የትናንቱን አስበን፣ የዛሬውን ኾነን እንዲሁም የነገውን አልመን መሥራት ተገቢ ነው” ብለዋል። ሰላም፣ ዕድገት እና ልማት በሁሉም ትብብር የሚመጣ ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ በዓሉን ስናከብር ልጃገረዶች ለሰላም፣ ዕድገት እና ብልጽግና የበኩላቸውን ሚና እንዲያበረክቱ ብሎም ድምጻቸው እንዲሰማ በማሰብ መኾን አለበትም ነው ያሉት።

በአማራ ክልል ዛሬም የልጅነት ጋብቻ አልተቀረፈም፤ ጾታ ተኮር ጥቃት አልቆመም ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ ለሴቶች ክብር አለመሥጠት እና ማሸማቀቅ አሁንም አለ ነው ያሉት። ስለዚህ የጾታ ዕኩልነትን በሁሉም መስክ ማስፈን ካልተቻለ የዴሞክራሲ ዕሴቶች ጎደሎ ይኾናሉ ብለዋል።

እንደ ሀገር የሚገነባው ዴሞክራሲ የሴቶችን ተሳትፎ ሳያገልል፣ ድምጻቸውን ችላ ሳይል፣ ተጠያቂነትን ያሰፈነ ከኾነ ፍትሐዊነትን፣ አካታችነትን እና ዕኩልነትን ያሰፍናል ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ሴቶች በዕኩል የሚጠቀሙበትን አሠራር ማሰብ እና መተግበር የግድ ነው።

መንግሥት ታዳጊ ሴቶች ላይ መሥራት የነገን የተሻለ ሀገር መገንባት መኾኑን ቀደም ብሎ በመገንዘብ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል። በቀጣይም ውስንነቶችን ለማስተካከል ከአጋር አካላት ጋር በትብብር ይሠራል ነው ያሉት።

ዶክተር ሙሉነሽ አክለውም በትምህርት ረገድ በአንደኛ ደረጃ በተማሪ እና መምህራን የሴቶች ቁጥር ከፍ ያለ ሲኾን ወደ ላይኛው ዕርከን ሲወጣ ግን ውስንነት አለ ነው ያሉት። ስለዚህ ጥሩ ተመክሮዎችን በማጠናከር እና በማስፋፋት ውስንነቶችን ማረም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው ነገ ተስፋ ነው፤ ተስፋ ደግሞ ሕይወት ነው፤ ነገን ለትልቅ ቦታ ያለመ ዛሬ ላይ ተመስርቶ መሥራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት። ሕጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ሲሰራ የምንመኛትን ለኑሮ ምቹ የኾነች የበለጸገች ሀገር መገንባት ይቻላል ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን የህጻናት መብት እና ደኅንነትን መጠበቅ ደግሞ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚሻ የሀገር ኀልውና ነው ብለዋል።

ቢሮ ኀላፊዋ አክለውም የልጃገረዶች ቀን ሲከበር ከህጻናት ቁጥር ግማሹን የሚሸፍኑት በተዛቡ አመለካከቶች ምክንያት ለችግር ተጋላጭ የኾኑ ልጆች ጉዳይን በማሰብ መኾን አለበት ነው ያሉት። የታዳጊ ልጃገረዶችን ችግሮች ለማስወገድ አጋር አካላትን በማስተባበር የልጆችን መብቶች ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላል ብለዋል።

ልጃገረዶች አሁንም ለተለያዩ ችግሮች ሲጋለጡ ይታያሉ ያሉት ኀላፊዋ የልጆችን መብት እና ደኅንነት መጠበቅ የሁሉም ኀብረተሰብ ኀላፊነት ነው ብለዋል። መንግሥት ሴቶችን በማብቃት እና ደኅንነታቸውን ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ መኾኑን በመገንዘብ የሴቶችን ዕኩልነትን ለማስፈን በመትጋት ለውጥ እያስመዘገበ መኾኑን ወይዘሮ ብርቱካን ተናግረዋል።

የልጃገረዶች ቀን ሲከበር የአማራ ክልል በገጠመው ችግር ምክንያት በርካታ ልጃገረድ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ስለኾኑ እነዚህን ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ ቢሮ ኀላፊዋ ጠይቀዋል።

በዓሉ የተከበረው የታዳጊ ልጃገረዶችን መብትና ደህንነት በማስከበር፣ ጤነኛ፣ በስነምግባር የታነጹ ተወዳዳሪ ዜጎች ለማድረግ ከቤተሰብ ጀምሮ የበርካታ አካለትን ርብርበ የሚጠይቅ ቢሆንም በተለይ የትምህርት ፣ ጤና፣ የፍትህና፣ የሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ተቋማት ከሌሎች አጋር እና ባለድርሻ ጋር በቅንጅት ምን እየሰሩ ያሉትን ተግባራት እና ያጋጠሙ ችግሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ከጤና ቢሮ ዶር. ትእግስት ብሩ ፣ ከፍትህ አቶ እሸቱ አለነ፣ከትምህርት አቶ ይገርማል አያሌው እንዲሁም ከሴቶች ፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ወ/ሮ ደስታ ፈንታ የተሳተፉበት የፓናል ውይይት በማካሄድ እና የታዳጊ ልጃገረዶችን የህይወት ልምድ በማካፈል ሲሆን በመድረኩ የተሳተፉ ታዳጊ ልጃገረዶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የታዳጊ ልጃገረዶችን መብትና ደህንነት በማስጠበቅ ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ያግዛሉ ያሏቸውን ሀሳብ አስተያየቶች እንዲሁም ጥያቄዎች በማንሳት በፓናል ተወያዮችና በሌሎች የሚመለከታቸው ተሳታፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ፕሮግራሙን መልእክት አስተላልፈው የዘጉት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ዝና ጌታቸው የታዳጊ ልጃገረዶችን መብትና ደህንነት በማስከበር፣ ጤነኛ፣ በስነምግባር የታነጹ ተወዳዳሪ ዜጎች በመፍጠር የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች እና መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ርብርብ የሚሻ ጠንካራ ቅንጅት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ኃላፊዋ አያይዘውም የታዳጊ ኅጻናትን ቀን በአሉን አንድ ቀን አክብሮ መዋል ሳይሆን ሁልጊዜም እና መቼም ስለህጻናት፣ ስለህጻና እና ታዳጊዎች እያሰቡ በእነሱ ላይ መስራት ካልተቻለ የሚፈለገውን ልማትና ብልጽግና ማረጋገጥ አይቻልም ብለዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top