ተቋማት ለአካቶ ትግበራ የተለየ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እያደረገ ያለው የድጋፍ፣ የክትትል እና የማብቃት ስራ ይበል የሚያስብል ነው፡፡/የተቋማት አካቶ ትግበራ መመዘኛ ማዕቀፍ ላይ ውይይት ያደረጉ የተቋማት ሃላፊዎች/
አማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮች ጋር በአዲሱ የተቋማት አካቶ ትግበራ መመዘኛ ማዕቀፍ ላይ ጥቅምት 22 /2017 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ውይይት አደረገ ፡፡
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ ተቋሙ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ ፣ በሁሉም መስክ የሚኖራቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲያድግ ፣የወጡ የህግ ማእቀፎች፣ስምምነቶች ተግባረዊ እንዲሆኑ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ተቋም እንደሆነ ጠቁመው
ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መካከል ተቋማት የሴቶችን፣ የህጻናትን፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካተው እንዲሰሩ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እገዛ፣ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ቁጥጥር ማድረግ በመሆኑ ይህንን ተግባር ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በተሻለ ለመፈጸም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ቢሮ ኃላፊዋ አያይዘውም ቢሮው ግንዛቤ ከመፍጠር፣ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ ተቋማት በአካቶ ትግበራ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ ምዘና ማድረግ እንደተጀመረ እና እስከ አሁንም በሁለት ዙር ወደ 25 ተቋማት በአዲሱ የመመዘኛ ማእቀፍ አማካኝነት መመዘናቸውን ገልጸው የመድረኩ አላማም ምዘናው በዙር የሚካሄዱ በመሆኑ በቀጣይ ለሚመዘኑ ተቋማት ሃላፊዎች የምዘና ማዕቀፍን በማስተዋወቅና አጠቃላይ በአካቶ ትግበራ ላይ ውይይት በማድረግ ለምዘናው አልፎም ለአካቶ ትግበራው ውጤታማነት አመራሩ በልዩ ትኩረት እንዲሰራ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ በሴቶች፤ህፃናት፤አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጉዳይ ማካተትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ሰለሞን ክንዱ አማካኝነት መመዘኛ ማዕቀፉንና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚዳስስ የውይይት መነሻ ጹሁፍ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ተሳታፊ የተቋማት አመራሮችም ምዘናውንም ሆነ የማካተት ተግባሩን ውጤታማ ያደርጋሉ ያሏቸውን ሃሳብ አስተያየቶች በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
አማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮተቋማት ለአካቶ ትግበራ የተለየ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እያደረገ ያለው የድጋፍ፣ የክትትል እና የማብቃት ስራ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎች በየተቋሙ ከምዘና ማዕቀፉ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎች፣ሃሳብ አስተያየቶችንም አንስተው ውይይቱን በመሩት በተቋሙ ምክትል ቢሮ ኃላፊ በወ/ሮ ዝና ጌታቸው እና በዳይሬክተሩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም ተቋማት በአዋጅ የተሰጣቸውን ተግባር እና ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት የሴቶችን፣ የህጻናትን፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ተቋሙ ተቋማት ለአካቶ ትግበራ የሚሰጡት ትኩረት እንዲያድግ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በሚል መግባባት ላይ ተደርሷል።
ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም
ባህር ዳር ከተማ



