ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር ለአካል ጉዳተኞችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ፡፡

አካል ጉዳተኞች እምቅ ዓቅማቸውንና ችሎታቸውን አውጥተው እንዲጠቀሙና ለልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንዲሁም ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ሥምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ የእነዚህን ሥምምነቶች ተፈጻሚነት እውን ለማድረግ የሀገሪቱ የህግ አካል ከማድረግ በተጨማሪ ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሌሎች መብቶቻቸውን የሚያስጠብቁ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች ወጥተዋል፡፡

በየደረጃው የሚገኘው የሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ተቋምም የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በበላይነት የሚያስተባብር እና ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የወጡ የህግ ማዕቀፎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ይከታተላል፡፡

መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከአካል ጉዳተኞች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን መስማት የተሳናቸው ሰዎች በምልክት መማር፣መግባባት ሀሳባቸውን መግለጽ እና የሌሎችን ሀሳብ መረዳት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የምልክት ቋንቋ ተደራሽት አነስተኛ በመሆኑ ከእነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ሲገድቧቸው ይስተዋላል፡፡ በተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍም የአብክመ ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከክልልና ዞን የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች የምልክት ቋንቋ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናው የተሰጠው በስፋት አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ተቋማት ለተውጣጡ 60 ሰልጣኞች ሲሆኑ ስልጠናው ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ በተጋበዙ የመስኩ ሙህራን ነው፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ተገኝተው ለሰልጣኖች መልእክት ያስተላለፉት የአብክመ ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ቢሮው በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አንስተው መስማት የተሳናቸውን አገልግሎት ከመስጠት አኳያ መሰረታዊ የሆነ ክፍተት ያለ በመሆኑ እና በለጉዳዮችም በተደጋጋሚ የሚጠይቁት የተቋማችንም ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ፈልገው ወደ ተቋማት ሲሄዱ በቀላሉ ለመግባባት እንዲሁም ችግሮቻቸውን ለመረዳትና ለመፍታት የተዘጋጀ ስልጠና እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ አያይዘውም ስልጠናው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና እንደሆነ እና በቀጣይም ከዩኒቨርስቲዎች ጋር በመነጋገር ቀጣይነት ባለው መንገድ የየተቋማቱን ባለሙያዎች የማብቃት ስራ እንደሚሰራ ገልጸው ለዚህ ስኬት ደግሞ የሴክተር ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሚና ትልቅ በመሆኑ ተቋማት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የስራ አካባቢ በመፍጠር የአካል ጉዳተኞችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሰልጣኞችም ስልጠናው እጅግ አስፈላጊ ነው ለሚመለከተው ሁሉ ተደራሽ መሆን አለበት መሰረተዊ እውቀት አግኝተንበታል ብለዋል፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top