የአብክመ ሴቶች፤ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት/ድርጅቶች ጋር ለ4ኛ ዙር ምክከር አደረገ፡፡

በአንድነት እና በቅንጅት በመሥራት ክልሉን ከገበባት ችግር ፈጥኖ ማውጣት እንደሚገባ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ህዳር 05/2017 ዓ/ም በባህር ዳር ከተማ ለአራተኛ ዙር የጋራ ፎረሙ ምክክር ተደርጓል።

መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ድርጅቶቹ የጋራ ፎረም መሥርተው በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸው ተመላክቷል። የጋራ ፎረሙ ዛሬ ምክክር ያደረገው ለአራተኛ ጊዜ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኀላፊ አታላይ ጥላሁን በአማራ ክልል ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ጀምሮ ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል። በሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ነው የተናገሩት። በተፈጠረው ጦርነት ቀዳሚ ተጎጂዎቹ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ናቸው ብለዋል።

በጋራ ካልተረባረብን በስተቀር ችግሩን አንፈተውም ነው ያሉት። በክልሉ አሁን ባለው ግጭት ምክንያት አሳሳቢና አስቸጋሪ ነገሮች በማኅበረሰቡ ላይ መድረሳቸውንም አንስተዋል። ማኅበራዊ ተጋላጭነት በስፋት መጨመሩንም ገልጸዋል። እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ተገቢውን ሰብዓዊ አገልግሎት መስጠት ይገባል ነው ያሉት። ሃብትን ማሰባሰብ እና በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል።

የጋራ የምክክር መድረኩ ለችግሮቹ የጋራ ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። የማኀበራዊ ተጋላጭነትን ለመከላከል ደግሞ ሁሉም በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሁላችንም ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔው አካል መኾን አለብን ብለዋል። ችግርን በችግር የማለፍ እንጂ ለችግሮች መፍትሔ የማበጀት ክፍተት መኖሩንም ገልጸዋል።

ማኅበራዊ ኀላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል። በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ላይ ጫና መኖሩን ነው የገለጹት።

መረጃዎችን በሚገባው በመያዝ በሁሉም አካባቢዎች ተዳራሽና ፍትሐዊ የኾኑ ሥራዎችን መሥራት ይገባል ብለዋል። የችግሩን መጠን መለየትና ከችግር ተነስቶ ምላሽ መስጠትና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ክልሉን ከገባበት ችግር እና ስብራት ለማውጣት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች በአንድነት እና በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ከስብራቱ ለመውጣት ሃብት ማሰባሰብ እና ድጋፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። መንግሥት ለሰላም በሰጠው ትኩረት ውጤቶች እየተገኙ መኾናቸውን የተናገሩት ኀላፊዋ ከሰላሙ ጎን ለጎን የልማትና የማኀበራዊ ሥራዎችን በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል። በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ የኾኑ ሕጻናት ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ሕጻናት እንዲማሩ ማድረግ፣ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መከላከል እንደሚገባም ገልጸዋል።

የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ጉዳይም በትኩረት ሊሠራበት የሚገባው ጉዳይ መኾኑን ነው የተናገሩት። ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። አንድነት እና ትስስር ካለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ገልጸዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top