የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለህጻናት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዓለም አቀፍ የህጻናትን ቀን አስመልክቶ ለህጻናት የመማሪያ ቁሳቁስ እና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉ የተደረገው በዐጼ ሰርጸ ድንግል መላክ ሰገድ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ ድጋፍ የሚሹ ህጻናት ነው።

የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በዓሉ በዓለም ለ35ኛ በሀገር ደረጃ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበር መኾኑን ገልጸው መሪ ሀሳቡም ”ህጻናት የሚሉት አላቸው፤ እናዳምጣቸው” የሚል መኾኑን ጠቅሰዋል።

ህጻናትን ማሳደግ ብቻ ሳይኾን የሚሉትንም እንስማቸው ያሉት ኀላፊዋ በእንግድነት ስሜት እንዲያዳምጡ ብቻ ሳይኾን እንዲናገሩ ማድረግም በእድገታቸው ላይ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ገልጸዋል።

ስለኾነም በየደረጃው ሥራ እየሠራን ሲኾን በዚህ ትምህርት ቤት ተገኝተን በዓሉን ስናከብር የመማሪያ ቁሳቁስ እና ሌሎች ድጋፎችንም እናደርጋለን ብለዋል።

ህጻናት ለወላጆቻቸው እና ለማኅበረሰቡ የሚነግሩን ካለ የምናዳምጣቸው ይኾናል ነው ያሉት። በቀጣይም ይህንን መደጋገፍ ምክንያት በማድረግ ከተማሪዎችም ከመምህራንም ጋር እየተመካከርን የህጻናትን ሀሳብ እናዳምጣለን ብለዋል።

የዐጼ ሰርጸ ድንግል መላክ ሰገድ መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ዓባይነህ የሺዋሥ ለተማሪዎቻችን ድጋፉ መደረጉ አስደስቶናል ብለዋል። ይህ ለተማሪዎቻችን ትልቅ ድጋፍ ነው፤ ለአካል ጉዳተኞችም የልብስ ድጋፉ ችግር ፈቺ መኾኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ለዓይነ ስውራን ተማሪዎች ወርሃዊ የቤት ኪራይ ክፍያ ቢሸፈንላቸው የኢኮኖሚ ችግራቸው ይቀረፋል ነው ያሉት። በትምህርት ቤቱ የተጀመረው የምገባ ፕሮግራምም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ክትትል ቢደረግበት ብለዋል።

የድጋፉ ተጠቃሚ ተማሪ ዮናስ ተሻገር አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ደብተር ይሰጡ ነበር አሁን ደግሞ ብርድ ልብስ መሰጠቱ ጥሩ ነው ብሏል። ለኛም በተደረገልን የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ደብተር በበቂ ስላገኘን ለመማሪያ አንቸገርም፤ ቤተሰቦቻችንም እንዳናስቸግር ያደርገናል ብሏል።

ተማሪ ሂሩት ሰማኸኝ በበኩሏ በተደረገው ድጋፍ ደስተኛ እንደኾነች ገልጻለች። በየዓመቱ የትምህርት ድጋፍ መደረጉም በቁሳቁስ እንዳናስብ አድርጎናል ብላለች።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top