‎‎በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 53 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የህበረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል- ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

‎(ባህርዳር፣ ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም) “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ፬” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየው የ2017 የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማጠናቀቂያ እና የእውቅና መርሐ ግብር ተካሄደ፡፡

‎የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በመርሐግብሩ እንደገለፁት በ2017 የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት 53 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የህበረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

‎በአገልግሎቱም በመንግስትና በማህበረሰቡ ያልተሸፈኑ ከ56 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የልማት ሥራዎችንና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማከናወን መቻሉንም ተናግረዋል።

‎የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ በሀገራችን የወጣቶችን እና የሴቶችን ሁለገብ ተሳትፎን ለማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከሚካሄዱ ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎ይህም በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ድልድይ በመሆን እና እየተዳከሙ የነበሩ ማህበራዊ እሴቶቻችን መልሰው እንዲዳብሩ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

‎በተጨማሪም በክረምቱ ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በህዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ እና ከውጤቱም ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን የተሰሩ የልማት ስራዎችንም ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት እንዲጠብቅ እና እንዲንከባከብም በቅንጅት መሠራቱን ገልፀዋል።

‎በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ዘንድ ሀገራዊ አንድነት እንዲፈጠር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቁመዋል።

‎አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ የወጣቶች እና የሴቶች ሚና አስተዋጽኦ እጅግ የላቀ በመሆኑ አሁን ያለውን ለውጥ፣ እድገናት የመደጋገፍ ባህል ቀጣይነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

‎በተለይ መጪው ሀገራዊ ምርጫ እንደመሆኑ በጎ ፈቃደኞች በማስተባበር እና ሰላማዊ ምርጫ ምህዳር እንዲፈጠር በማደረግ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እና የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top