የዘንድሮው ዓለም-አቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀናት የንቅናቄ መርሐግብር ማስፈፀሚያ ሀገራዊ ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሂክማ ኸይረዲን በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈፀም ፆታዊ ጥቃት ለተደራራቢ ጉዳት እየዳረገ በመሆኑ ድርጊቱን ከማውገዝና መከላከል ባሻገር ለጎጂዎች ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
እስካሁን በመንግስትና አጋር አካላት የጋራ ጥረት ድርጊቱን ለመከላከል የሚያግዙ በርካታ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም በማወቅም ሆነ በግንዛቤ ማነስ፣ ከቅንጅታዊ አሰራር መላላት፣ ከህግ አፈጻጸም ክፍተት ጋር በተያያዘ ድርጊቱ እየተፈጸመ ያለበት ሁኔታ በመኖሩ የተጀመረውን ርብርብ የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ማለት አስገንዝበዋል፡፡
ዘንድሮ በብሔራዊ ደረጃ ጾታዊ ጥቃትን የማስቆም ዓላማን ማዕከል ያደረጉ ሰፋፊ የግንዛቤና ንቅናቄ ስራዎችን ለማካሄድ እና ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶችና ህፃናትም ድጋፍና ተጨባጭ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱን ነው የገለፁት።
በተጨማሪም ህዳር 11 የሚከበረው አለም አቀፉ የህፃናት ቀን ምክንያት በማድረግ የህብረተሰቡንና የባለድርሻ አካላት ግንዛቤና ተሳትፎን በማጎልበት የህፃናት፣ መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ ሁነቱቶቹን ለማስፈፀም የተዘጋጀው ሀገራዊ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት በማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በመርሐግብሩ ከፌደራል ሴክተር መ/ቤቶች የአካቶ ትግበራ ዳይሬክተሮች እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስርዓተ ጾታ ዳይሬክተሮች እንዲሁም ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የውጣጡ ባለድርሻና አጋር አካላት ተገኝተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር



