የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች፣ የህጻናት፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ ፣ በሁሉም መስክ የሚኖራቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲያድግ ፣ የወጡ የህግ ማእቀፎች ፣ ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መካከል ተቋማት የሴቶችን፣ የህጻናትን፣ የአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካተው እንዲሰሩ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እገዛ፣ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ቁጥጥር ማድረግ በመሆኑ ይህንን ተግባር ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በተሻለ ለመፈጸም ከተቋማት አመራሮችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በመፍጠር፣ተግባሩን ለማሳለጥና ሁሉም ተቋማት ወጥ በሆነ መልኩ ዘላቂነት ያለው ተግባር እንዲፈጽሙ የሚያስችል ሰነዶችን በማዘጋጀት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከክልል የመንግስት ቢሮዎች ከተውጣጡ አመራሮች ጋር በአዲሱ የተቋማት አካቶ ትግበራ መመዘኛ ማዕቀፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ጥቅምት 15/2018 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ አካሄዷል፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ በመፈጸም የተቋሙ ደንበኞች በሁሉም መስክ የሚኖራቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲያድግ መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የተቋማት እገዛ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ቢሮ ኃላፊዋ አያይዘውም ቢሮው ግንዛቤ ከመፍጠር፣ ድጋፍና ክትትል ከማድረግ በተጨማሪ ተቋማት በአካቶ ትግበራ ያሉበትን ደረጃ ለማወቅ በአካቶ ትግበራ መመዘኛ ማእቀፍና ሌሎች ሰነዶች ከመስጠት ባለፈ ምዘና ማድረግ እንደተጀመረ ባለፈው በጀት አመት ወደ 40 ቢሮዎች በአዲሱ የመመዘኛ ማእቀፍ አማካኝነት መመዘናቸውን ውጤታቸውንም ይፋ ማድረጋቸውን ገልጸው
የመድረኩ ዋና አላማም ምዘናው ለ2ኛ ዙር ከሚመዘኑ ተቋማት አመራሮች ጋር በአካቶ ትግበራና በምዘና ማዕቀፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ግልጽ ውይይት በማድረግ በማድረግ ምዘናውን በእውቀት ላይ ተመስርተው በውጤታማነት እንዲያከናዉኑ አልፎም ለአካቶ ትግበራው ውጤታማነት በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ በማድረግ ለሴቶችን፣ ህጻናትን፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች መብትና ደህንነት መጠበቅ ተሳትፎና ተጠቃሚነት መረጋገጥ ያለባቸውን ተቋማዊና የዜግነት ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ይህን አላማ ለማሳካትም ከምንጊዜውም በላይ ከተቋማት ጋር በጠንካራ ቅንጅት እንደሚሰሩም እና ለሌሎች ቀሪ ተቋማትም ተመሳሳይ መድረክ በቀጣይ እንደሚካሄድ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ በሴቶች፤ህፃናት፤አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ጉዳይ ማካተትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ ሰለሞን ክንዱ አማካኝነት ቀርቦ እና ምዘናውን በሚያስተባብረው እና በሚመዘኑ ተቋማት ላይ ያሉ መልካም ጅማሮዎችን እና ለአሰራር ችግር ናቸው የሚሏቸውን ነጥቦች እና የግልጽነት ጥያቄዎች በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች ተቋሙ ተቋማት ለአካቶ ትግበራ የሚሰጡት ትኩረት እንዲያድግ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበው ተቋማቸውን በመመዘን በምዘናው ውጤት መሰረት ችግራቸውን በመለየት የማስተካከያ እርምት ለመውሰድ የሚያስችላቸው ግንዛቤ እንዳገኙ እና ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከሚመደብላቸው ባለሙያ ጋር በመተባበር እስከ ህዳር 3/2018 ዓ.ም ድረስ ተቋማቸውን መዝነው እንደሚያሳዉቁ መግባባት ላይ በመድረስ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡




