የአብክመ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በዩኒሴፍ የልጅነት ጋብቻ ይቁም ፕሮግራም በሚተገበርባቸው ወረዳዎች ለተውጣጡ የሴቶች ግንዛቤ ንቅናቄና ተሳትፎ እንዲሁም ለህጻናት መብትና ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪዎች፣ ባለሙያዎችና የፕሮግራም አስተባባሪዎች በልጅነት ጋብቻ እና በሴት ልጅ ግርዛት ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ከመስከረም 9 እስከ መስከረም 10/ 2017ዓ/ም በባህርዳር ከተማ ሰጠ።
እንደ ሀገር የልጅነት ጋብቻ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቆም የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ ፣ በጎጅ ልማዳዊ ድርጊት ዙሪያ በተዘጋጀው የማህበረሰብ ውይይት ማንዋል እንዲሁም ከትምህርት ቤት ውጭ ያሉ የልጃገረዶች ክበብ አደረጃጀትና ተግባራት የስልጠናው ዋናዋና ርእሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡
እንደ ክልል የልጅነት ጋብቻና ተያያሽ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን በ2017 ነጻ ለማድረግ የአብክመ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እና ለውጥም እያስመዘገበ ቢሆንም በሚፈለገው ልክ ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ ግን በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ማነቆዎች እንደሆኑ በስልጠናው ተገልጿል።
በስልጠናው ማጠቃለያም በቢሮው የህጻናት መብት ደህንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዴ እንዲሁም የሴቶች ግንዛቤ፣ ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር ወ/ሮ ደስታ ፈንታ በችግር ውስጥ ብንሆንም ከአጋር አካለት እና ከአደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት በመስራት ግቡን ማሳካት እንደሚገባቸው በመግለጽ ሰልጣኞች ወደ ስራ ሲመለሱ ከወረዳ እስከ ቀበሌ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ማህበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት የሀይማኖት አባቶችን፣ አደረጃጀቶችንና ጥምረቶችን አቀናጅቶ የስልጠና እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ማስቀጠል፤ የተሰሩ ስራዎችን ሪፖርት በተቀመጠው ፎርማት መሰረት በተዋረድ መላክ እንደሚገባ የቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ሰልጣኞችም ስልጠናው ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትሎ ማህበረሰባዊ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ማህበረሰቡ ራሱ በማውገዝ ድርጊቱ የሚያስከትለውን አካላዊ፣ ስነልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በመረዳት ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶችን እንዲከላከል የግንዛቤ ስራን ለመፍጠር እውቀትና ልምድ አግኝተንበታል በቁርጠኝነትም የነበሩብንን ክፍተቶች በመሙላት ለተሻለ ውጤት እንተጋለን ብለዋል።
መስከረም 2017ዓ/ም
ባህር ዳር



