ሴትነት ምልዑነት ነው፡፡

በአባታችን አዳም ወደዚች ምድር መምጣት ምክንያት የሰው ልጅ በዚህ ምድር መኖር መጀመሩ የሚታወቅ ቢሆንም ቀጣይነቱና የህይወት ሙሉዕነት የተገኘው እና የተረጋገጠው ግን እናታችን ሄዋን ህልው መሆን ከጀመረችበት ጊዜ በኋላ ነው፡፡ የሰው ፍጥረት እንዲቀጥል “ብዙ ተባዙ” የሚለው አምላካዊ ቃሉ የተተገበረው በሄዋን መምጣት ነው፡፡

እዚህ ላይ ምናልባት አንዱ ለሌላው ያለው አስፈላጊነት የሚያጠያይቅ ባይሆንም የእናታችን ሄዋን መምጣት ግን ለዚህ ሁሉ ግኝት ዓይነተኛ ምክንያት ነው፡፡ ያለ ሴቶች መኖር የዓለምን ቀጣይነት መረጋጋጥ የሚሳነን መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በተያያዘም ያለ ሴቶች ምንም ነገር ሊሳካ አይችልም መባሉ እንዲሁ ለነሲብ ሳይሆን ሴቶች የህልውና መሰረት በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ያለው አንደምታ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ተፈጥሯዊ እውነታ ነው፡፡

ዛሬ ከ50 በመቶ በላይ የዓለማችን ህዝብ ሴቶች መሆናቸው ቁጥራዊ ንጽጽር ብቻ ሳይሆን የያዙትን ወሳኝ ድርሻ የሚያሳይ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ተፈጥሮ ለሴቶች የሰጠችውን ፀጋ ወንዶች ሊመኙትም ሆነ ሊያገኙት የሚቻል አይደለም፡፡ ይህንን ፀጋ ለማጣጣል የሚደረግ ሙከራም ካለ ካለዋቂነት የሚመነጭ ነው ፡፡

ዓለማችን ዛሬ የደረሰችባቸው የእድገትና የኑሮ ደረጃዎች ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሴቶች የጎላ ተሳትፎና አስተዋፅዖ ውጤት ነው፡፡ የምንኖርበት ዓለም ሴት ፈጥራ ወንድ የሚጠራበት ዘመን መሆኑ እንጂ ምንም ነገር ያለ ሴት የሆነም የሚሆንም የለም፡፡ ሴት ወልዳ በአባት መጣራቱ፣ እርሻን ሴት ፈልስፋ ወንድ አራሽ አንደፋራሽ ገበሬ ተብሎ መሞገሱ የተዛባ እይታ ቢሆንም ሴት ልጅ በሁሉም መስክ ወሳኝ ድርሻ ያላት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ከእያንዳንዱ ጠንካራና ሴኬታማ ወንድ ጅርባ ጠንካራ ሴት አለች የሚለውን ሀሳብ መገንዘብ ሊቅ የሚያሰኝ አይሆንም፡፡

በሌላ በኩል “ሴትን ማስተማር አገርን ማስተማር ነው” የሚለው አባባል እንዲሁ የተነገረ ሳይሆን ሴቶች የተሻለ እድል ባገኙ ቁጥር የሚፈጥሩት ተፅዕኖና የሚያመጡት ውጤት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ለአብነት አንድ የተማረች ሴትና ሌላ ያልተማረች ሴት ባለችበት ቤተሰቦች ውስጥ ሊኖር የሚችለውን ቤተሰባዊ እርካታና ውጤታማነት ስንመዝን ለውድድር የሚበቃ እንዳልሆነና የተማረች ሴት ባለችበት ቤተሰብ ውስጥ የሚገኘው ውጤት ደግሞ እጅግ ከፍተኛና ዘላቂነት ያለው መሆኑ እሙን ነው፡፡

በተያያዘም ሴት የሠላም መሠረት ናት፡፡ ልዩነቶችን በመቻቻል፣ በመነጋገርና የጋራ ጥቅምን በማስቀደም ከግጭት በራቀ መልኩ በሠላማዊ መንገድ መፍታት የምትፈልግ ነች፡፡ ሴት ልጅ ነገሮችን በአስተውሎት ከማየት ጀምሮ ወደ ችግር እንዳይለወጥ ማድረግና ከተለወጠም በንግግርና በሰጥቶ መቀበል መፍትሄ መስጠት የምትችል ፍጡር ነች፡፡

ሴት ልጅ አፍቃሪ ናት፡፡ ፍቅር የሁሉም ነገር መፍትሄ ነው፡፡ ዓለም ከጥፋት የዳነችውም ሆነ የምትድነው በፍቅር ነው፡፡ ሴቶች ጦርነትን አጥብቀው ከሚጠሉበት ዋናው ምክንያት የፍቅር ሰው በመሆናቸው ነው፡፡ ፍቅር ማለት እግዚአብሄር ነው የሚባለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ፍቅር መድሃኒት ነው፡፡ ሴቶች ፍቅር ናቸው፡፡ ስለሆነም ሴቶች የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሄና መድሃኒቶች ናቸው፡፡

በመሆኑም ዓላማችን ምሉዕ ሊሆን የሚችለው በሴቶች ተሳትፎና ወሳኝ ድርሻ እንዲይዙ በማድረግ ነው፡፡ ይሁንና አብዛኛው ተባዕት ይህንን የማወቅና ግንዛቤ የመወሰድ ችግር ይስተዋልበታል፡፡ የሴትን ልጅ ወሳኝ ድርሻ ካለመቀበል ጀምሮ ተፈጥሮ የሰጣትን ፀጋ ተገንዝቦ በአግባቡ ለመጠቀም ሲቸገርና አልፎ ተርፎም በሴቶች ላይ ችግር ሆነው መታየታቸው በተደጋጋሚ የሚታይ ሀቅ ነው፡፡

የሴችን ሀሳብ ባለመቀበል ትዳር ሲፈርስ፣ አገር ሲተራመስ እንደ አጠቃላይ ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር በማድረግ የወንዶች ድርሻ የላቀ ነው፡፡ ለአብነት፡- የዓለማችን የሠላም እጦት ምክንያት ከሰቶች ይልቅ ወንዶች ሆነው መታየታቸው ከዚሁ በመነጨ ነው፡፡

ከዚህ የከፋው ሌላው ነገር ግን ወንዶች ሴቶችን አክበረውና አዳምጠው ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ዜጋ ችግር ላለመሆን ከመጣር ይልቅ ሴቶች ላይ በሚፈጥሩት ችግር ሴቶችም ላይ ሆነ ሌላው ማህበረሰብ ጉዳት ማድረሳቸው ነው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች በግልጽ እንደሚያሳዩት የማህበራዊ ቀውስ ምክንያቱ የቤተሰብ ቀውስ ነው፡፡

የቤተሰብ ቀውስ በዋናነት መነሻው በሴቶች ላይ በሚደርስ ጥቃት ነው፡፡ ለዛም ነው በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በማህበረሰቡ ላይ የሚደርስ ጥቃት የሚሆነው፤ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በሁላችም ላይ የሚደርሰው፡፡ ስለሆነም ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አንዱ የሆነውን ፆታዊ ጥቃት መከላከልና ማውገዝ ከሁሉም ይጠበቃል። የሴቶችን ጥቃት መከላከል የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡

ሴቶችን መከላከል አገርን መከላከል ነው፡፡ ሴት ልጅ አገር ናትና፤

በአሁኑ ስዓት ዓላማችን የማህበረሰባችን ወሳኝ አካል የሆነችውን ሴት የሁሉም ፖሊሲዎች ዋነኛ አካል የማድረጉ አስፈላጊነት የሚያሳየው ነገር ቢኖር ሴቶችን ያላማከለ ፖሊሲ በየትኛውም መለኪያ ዘላቂ ጥቅም ሊያመጣ ስለማይችል ነው፡፡ የትምህርት ፖሊሲው ሴቶችን በከፍተኛ መጠንና ጥራት እንዲማሩና አገርን እንዲመሩ ማድረግ ካልቻለ፣ የጤና ፖሊሲው የሴቶችን ጤና ቅድሚያ መስጠት የማያስችል ከሆነ፤ የተለያዩ የልማት ፖሊሲዎች ሴቶችን ወደፊት እንዲመጡ ማገዝ ካልቻለ ከወረቀት ያለፈ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም፡፡

በተያያዘም የዓለማችን ፖለቲካ ቅድሚያውንና የመሪነቱን ሚና ሴቶች ካልወሰዱ ዘላቂ ሠላምና ልማትን ማረጋገጥ የሚቻል አይሆንም፡፡ ስለሆነም ‘የሴቷ ጥቃት የእኔም ጥቃት ነው’ በማለት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሴቶችን ጥቃት ከመከላከል ባሻገር ሴቶችን የሁሉም ተግባራት ማዕከል ማድረግን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

በመጨረሻም የዓለማችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው በሁሉም ረገድ የሴቶችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲቻል መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ይህም መሆን አለበት ሲባል ጉዳዩ ሴቶች በተናጠል ተጠቃሚ ለማድረግ ሳይሆን ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ በመሆኑ ነው፡፡ ከላይ በርዕሱ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ሴትነት ምልዑነት ስለሆነ ነው፡፡

ሴቶችን አከብራለሁ፤ ጥቅሞቻቸውን አስከብራለሁ፤ጥቃታቸውንም እከላከላለሁ፤

የሴቷ ጥቃት የእኔም ጥቃት ነው፡፡

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top