የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ
ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ለአስከፊ ድህነት ሊዳረጉ ይችላሉ:: መሰረታዊ አጋላጭ ምክንያቶች የሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሲሆኑ የአካባቢ መራቆትና የሚያስከትለው የምግብ ዋስትናን የማጣት ችግር፣ የአየር ንብረት መዛባትና እሱን ተከትሎ የሚመጣ ድርቅና የኢኮኖሚ መዛባት ችግር፣ ጦርነትና ግጭቶች የሚያስከትሉት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መናጋት ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡
ለእነዚህ ተጋላጮች አስተማማኝ የማህበራዊ ድጋፍ ካልተደረገላቸው በተለያዩ የአስከፊ ድህነት መገለጫ ለሆኑ በተለይም መጠለያ አልባ የመሆንና መደበኛ ባልሆን መጠለያ የመኖር፣ ከመኖሪያ አካባቢ የመፍለስና በጊዚያዊ መጠለያ የመጠለል፣ ለሴተኛ አዳሪነት የመዳረግ፣ ወደ ጎዳና የመውጣት፣ ወደ ልመና የመግባት ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡
ዜጎችን ከአስከፊ ድህነት ለመታደግና እሱን ተከትሎ ከሚመጣ ችግር ለመከላከል የተለያዩ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች መተግብር ግድ ይላል፡፡ በሀገራችንም በብሄራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መተግበር አንድ እርምጃ ወደፊት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ፡፡ የፖሊሲው የትግበራ ሂደት ከሞላ ጎደል የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ተጀምሯል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በገጠርና ከተማ የማህበራዊ ሴፍቲኔት ፤ የመንግስትና የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ ዋስትና ፤ በክፍያና ከክፍያ ነፃ የጤና መድን አገልግሎቶች እና የተሸከርካሪ የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ አገልግሎቶች፣ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ምላሽ ፣ የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በጅምር ደረጃም ሆነ ከከፊል እስከ ሙሉ በሙሉ የሚተገበሩ የምላሽ አሰጣጥ ፕሮግራሞችን መጥቀስ ይቻላል ፡፡
በሌላ በኩል ተጋላጮቹ ከዓይነታዊ ድጋፍ ባለፈ የአዕምሮ ጤና እና የስነልቦና ድጋፎች በመደበኛና በፕሮግራም እንዲያገኙ የማስቻል ተግባራት በየደረጃው እየተፈፀሙ ይገኛል፡፡
የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮም ለስሜን ሸዋ ዞንና ምንጀር ሸንከራ ወረዳ የሚመለከታቸው አካላት የአደጋ ሞላሸ የገንዘብ ድጋፍ ማስጀመሪያ ስልጠና ሰሞኑን በደብረብርሃን ከተማ ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ንጹህ ሽፈራው እንደገለጹት ስልጠናው ዜጎችን ከአስከፊ ድህነት ለመታደግና እሱን ተከትሎ ከሚመጣ ችግር ለመከላከል ከሚያስችሉ ፕሮግራሞች መካከል በአደጋ ምላሽ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ዓላማውም ፕሮግራሙን ለሚያስተባብሩ አካላት ግንዛቤ በመፍጠር ስራውን ማስጀመር ነው፡፡
ተቋሙ አሁን ካለው የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጋር ተያይዞ አስቸኳይ ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በርካታ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለሁሉም ተደራሽ ሆኗል ማለት ባይቻልም በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ሃላፊዋ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ከተረጅነት ወደ ራስ መቻል ጉዟችን ማሳከኪያዎች ናቸው ብለዋል፡፡
የማህበራዊ ጥበቃ ሽፋንን ተደራሽነት ማረጋገጥ የህይወት ቀጣይነትን ማረጋገጥ ነው ያሉት የቢሮው የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይነው ጸጋ የአደጋ ምላሽ የገንዘብ ድጋፍ ፕሮግራም ከዚህ በፊት በሶስት ዙር ማለትም በ1ኛው ዙር ፡- ብቸና፣ ፍኖተ ስላም እና አየሁ ጓጉሣ በ2ኛው ዙር እብናት፣ ቃሉ እና ጋዞ በ3ኛው ዙር ምንጃራ ሸንኮራ፣ ወገራ እና መራዊ እየተተገበረ እንደሆነ ፣ ስልጠናው 4ኛ ዙር በስሜን ሸዋ ዞንና ምንጀር ሸንከራ ለማስጀመር የሚካሄድ እንደሆነ እና
የስልጠናው ተሳታፊዎችም ለስሜን ሸዋ ዞንና ምንጀር ሸንከራ ወረዳ የሴቶች ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊዎች ፣ ቡድን መሪዎች ባለሙያዎች፣ የዞንና ወረዳ ገንዘብ መምሪያ /ጽ/ቤት ሃላፊዎች፣ የጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ አስተዳደሪ/ተወካይ/ ፣የምግብ ዋስትና ተወካዬች እንዲሁም መረጃ የሚሠበሰቡ በጐፈቃደኛች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡


