“በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የመከላከል እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ሥራ ላይ በስፋት እንሠራለን” የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ስሪአር ሲኤሲኢ ከተሰኘ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች መልሶ ማቋቋም እና ወደ ሥራ ማስገባት ላይ ያለመ የውይይት መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ አካሄዷል።

‎በመድረኩ የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ፣ የአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር)፣ የዞን እና የወረዳ ሥራ እና ሥልጠና መምሪያ ኀላፊዎች እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

‎አሚኮ ያነጋገራቸው የዞን እና የወረዳ ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ አሁንም ባለው የሰላም እጦት ምክንያት በርካታ ሴቶች ተጎጂ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በጾታዊ ጥቃት እና በሌሎች ምክንያቶች ተጎጂ የኾኑ ሴቶችን መልሶ በማቋቋም ረገድ ፕሮጀክቱ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑንም ነው ኀላፊዎቹ የተናገሩት።

‎የስሪ አር ሲኤ ሲኢ ፕሮጀክት አስተባባሪ መሐመድ ኡመር ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመት የሚቆይ መኾኑን አንስተው በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ ማቋቋም፣ አገልግሎቶችን ማሻሻል እና የግንዛቤ ፈጠራ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ መኾኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አባተ ጌታሁን (ዶ.ር) መድረኩ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በመለየት ሥልጠና ለመስጠት እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ስለመኾኑ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ፕሮጀክቱ የሚተገበረው 20 ወረዳዎች ላይ ሲኾን በስራቸው ባሉ 348 ቀበሌዎች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ነው ብለዋል።

በዚህ ዓመት ፕሮጀክቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ የማድረግ እና በአጠቃላይ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የመከላከል እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ሥራ ላይ በስፋት ይሠራል ነው ያሉት።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top