የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሞዴል የሴቶች የልማት ኅብረቶችን ለመፍጠር ያለመ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
መድረኩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በአደረጃጀት መፍታት ላይ ያተኮረ ነው። ከዚህ በፊት የነበሩ የአደረጃጀት ክፍተቶችን አሻሽሎ አተገባበራቸው ላይ በአጽንኦት መሥራትንም ያለመ ነው።
በምክክር መድረኩ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና ዓቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)፣ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ዝና ጌታቸው የመድረኩ ዓላማ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ሞዴል የሴቶች ልማት ኅብረት ለመፍጠር ነው ብለዋል።
የልማት ኅብረቱ ሴቶች ተሞክሯቸውን በመለዋወጥ እና በመደጋገፍ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ወሳኝነት አለው ነው ያሉት።
ሴቶች በአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት፣ በእንስሳት እርባታ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፎች እና ሌሎችንም ጸጋዎችን በመጠቀም ኑሯቸውን እንዲቀይሩ፣ የሚያጋጥማቸውን የበጀት፣ የግብዓት እና የሕግ አገልግሎት እጥረቶች እንዲፈቱ መታገዝ አለባቸው ብለዋል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ አደረጃጀቶች ሊፈጠሩ እንደሚገባ ነው ያብራሩት።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የልማት ኀብረቶች የጋራ ዓላማ እና ግብ ያላቸው እና በአንድ ቀበሌ ውስጥ በተቀራረበ መልክዓ ምድራዊ የጉርብትና ምኅዳር ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በየዘርፉ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሣትፎ እና ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማሳደግ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ይህን ሥራ የበለጠ በማጠናከር በልማት ሞዴል የኾኑ ሴቶችን ቁጥር ለማብዛት የአደረጃጀት ለውጦች እንደ ሀገር እየተሠራ እንደኾነም ገልጸዋል።
ሴቶች ላይ መሥራት ለቤተሰብ፣ ለማኅበረሰብ እና ለሀገር መሥራት ነው ያሉት ኀላፊዋ በተለይ ሴቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲኾኑ የገንዘብ ተቋማት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አቅም እንዲኾኑ አስገንዝበዋል።
ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ከተናጠል ይልቅ በተደራጀ አግባብ ማሳተፍ ይገባል ነው ያሉት።
በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ በቁጠባ ባሕል ኑሮን በማሻሻል፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን እና የኃይል ጥቃቶችን በመከላከል፣ አካባቢን እና የተፈጥሮ ሐብትን በመንከባከብ በሌሎችም ዘርፎች የሴቶችን ተሣትፎ እና ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) የገጠሙንን ማኅበራዊ ቀውሶች መሻገር የሚቻለው የችግሮችን መነሻ ለይቶ ለመፍትሄ በመሥራት እንደኾነ ገልጸዋል። ሴቶች ላይ የሥነ ልቦና ጫና የፈጠሩ፣ ተጠቃሚነታቸውን የጎዱ ማኅበራዊ ስብራቶች በዚህ ወቅት ተፈጥረዋል ነው ያሉት።
ይህን መቀየር የሚቻለውም በጋራ እና በትብብር ሴቶች ተጠቃሚነት ላይ በመሥራት ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ባለፉት ጊዜያት የተደራጀ የሕዝብ አቅምን በማሳደግ፣ ሴቶችን በየደረጃው ተሳታፊ እና ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት መሠራታቸውን ተናግረዋል።
የተሻሻለው የሴቶች የልማት ጥምረት አሠራር እና አደረጃጀት ወቅቱን እና ሕዝባችንን የሚመስል እና የሚመጥን ኾኖ እንደ ተደራጀም አቶ ይርጋ ገልጸዋል።
የሴቶች የልማት ኅብረት ጥምረት የልማት፣ የመልካም አሥተዳደር፣ የዴሞክራሲ እና የሰላም አጀንዳዎችን በመፈጸም እና በማሳለጥ ረገድ የሚኖራቸው ጠቀሜታ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡



