የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን “የተደራጀ የሴቶች ተሳትፎ ለሰላም እና ለዴሞክራሲ” በሚል መሪ መልዕክት 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን የካቲት 2/2017 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ አካሄዷል፡፡
በጉባኤው ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የርዕሰ መሥተዳድሩ የሕዝብ ግንኙነት እና አደረጃጀት አማካሪ ይርጋ ሲሳይ እንዲኹም የሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
በጉባኤው ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን በውስጥ የሴቶች ማኅበራት እና አደረጃጀቶችን አካትቶ የያዘ ፌዴሬሽን ነው ብለዋል።
በመኾኑም ዘርፈ ብዙ ፍላጎቶች ያሉት፣ እነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት ደግሞ ጠንክሮ እየሠራ ያለ ፌዴሬሽን ስለመኾኑ ተናግረዋል።
የሴቶች አደረጃጀቶች የቆሙለትን አላማ በምን ያህል መጠን እና ጥራት እንዳሳኩ በመከታተል እና በመገምገም ለበለጠ ውጤታማነት የሚያበቃ የወደፊት አቅጣጫ ማስቀመጥ እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ርእሰ መሥተዳደሩ አሳስበዋል።
የሴቶችን መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ከሁሉም ቀዳሚው ሥራ ነው፤ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የመኾን መብታቸው እንዲረጋገጥ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል።
ሴቶች በፖለቲካዊ እና በሌሎችም ዘርፎች እኩል ተሳታፊ እንዲኾኑም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳደሩ በኢኮኖሚው መስክ ተሳታፊ መኾን ያልቻሉ ሴቶች በፖለቲካው እና በሌሎችም ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ የሰመረ ተሳትፎ ሊኖራቸው አይችልም፤ ስለዚህ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ሥራ መኾን አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
የሴቶች ማኅበራዊ ተሳትፎ በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ የበለጠ ማደግ አለበትም ብለዋል። የሴቶችን ተሳትፎ ዝቅ የሚያደርጉ አስተሳሰቦችን መድፈቅ፣ እኩልነታቸውን እና ተጠቃሚነታቸውን የሚያጎለብቱ አስተሳሰቦችን ደግሞ የበለጠ ማዳበር ይገባል ነው ያሉት።
የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ በሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በአሥተዳደራዊ መዋቅሮች እና በባሕላዊ አደረጃጀቶች ጭምር ያለውን ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን የክልሉ ሴቶች በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲኾኑ ለማስቻል የማንቃት እና የማብቃት ሥራውን በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል።
ሰላም በሌለበት አካባቢ እና ሀገር ውስጥ የሴቶች መብት እና ጥቅም ይጎዳል፤ በመኾኑም ሴቶች በተናጠልም ኾነ በየአደረጃጀቶቻቸው ለሰላም ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳደሩ።
በዚህ ጉባኤ ላይ በሴቶች ማኅበራት ላይ የነበሩ ተግዳሮቶች ተነስተው ምክክር እንዲደረግ እና ተጨባጭ የመፍትሔ አቅጣጫዎችም እንዲቀመጡ አሳስበዋል። የክልሉ መንግሥት ሴቶችን አካታች የኾነ ልማት እንዲረጋገጥ ቁርጠኛ እንደኾነ ገልጸው ለዚህም ለሁሉም የሴት አደረጃጀቶች አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።


