የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን የካቲት 2/2017 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ አካሄዷል፡፡
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶች ያልተሳተፉባቸው እና ተጠቃሚ የማይኾኑባቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ናቸው ብለዋል። በግማሽ ጥረት ላይ የተመሠረቱ በመኾናቸውም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ለማምጣት አስቸጋሪ እንደኾነም አስገንዝበዋል።
“ሴቶችን በልማት ላይ ማሳተፍ የዕድገት እና የህልውና ጉዳይ ነው” ያሉት ቢሮ ኀላፊዋ ታላሚውን የልማት ግብ ለማሳካት አካታች ተሳትፎ እና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዘመናት በነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች ምክንያት ሴቶች ለሀገር ማበርከት የሚገባቸው አስተዋጽኦ ተገድቦ ቆይቷል፤ ተጠቃሚነታቸውንም ተነፍገው ኖረዋል፤ ይልቁንም የተለያዩ በደል እና ግፎችን ሲያስተናግዱ ቆይተዋል ነው ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ያለሴቶች ተሳትፎ የሚሰምር ልማት እንደማይኖር ታምኖበታል ብለዋል። የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማጎልበትም በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መኾኑን ተናግረዋል።
ቢሮ ኀላፊዋ እንዳሉት በአማራ ክልል ለሴቶች በተፈጠረው ምቹ ፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፍ በመጠቀም በመረጡት ዓላማ ተደራጅተው ለላቀ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት መብቃታቸውን ጠቁመዋል። በገጠሩ የግብርና ዘርፍ የመሬት ባለቤትነት ኢኮኖሚያዊ መብታቸው ተረጋግጧል ብለዋል።
የትምህርት፣ የጤና እና የሌሎችም ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑም በልዩ አቅጣጫ እየተሠራ ስለመኾኑ ቢሮ ኀላፊዋ ጠቁመዋል። በፖለቲካው ዘርፍም የመምረጥ እና የመመረጥ መብታቸው እንዲረጋገጥ መሥራትን ጨምሮ በተለያዩ የአመራር ሰጭነት ቦታዎች እንዲሳተፉ ሰፊ ሥራ መከናወኑን ወይዘሮ ብርቱካን አብራርተዋል።
ከተመዘገቡ ለውጦች ጎን ለጎን አሁንም ድረስ ተግዳሮቶች እንዳሉ ጠቁመዋል። የሴቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ አነስተኛ መኾኑ፣ የኢኮኖሚ አቅማቸውን የማሳደግ ውስንነት፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በሚፈለገው ልክ አለመድረስ፣ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ጥቃቶች ገና ያልተሻገርናቸው ሳንካዎች ናቸው ብለዋል። የሚወጡ ሕጎች በአግባቡ ተፈጻሚ ያለመኾን እና ጾታዊ ጥቃት በሚፈጽሙት ላይ አስተማሪ ርምጃ አለመውሰድም እንደ ችግር ተነስቷል።
እነዚህን በሴቶች ላይ የተደቀኑ ችግሮች በቅንጅት መፍታት ግድ እንደሚልም አሳስበዋል። ከ1 ሚሊዮን 845 ሺህ በላይ አባላትን የያዘው የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽንም ሴቶች በተለያዩ አደረጃጀቶች በመቀናጀት ለመብቶቻቸው እንዲቆሙ የሚያበቃ እና የሚያነቃ መኾን አንዳለበት አስገንዝበዋል።
ፌዴሬሽኑ የሴቶችን መብት እና ደኅንነት የማስጠበቅ ታላቅ ራዕይ ይዞ የሚንቀሳቀስ መኾኑን በመገንዘብ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በ3ኛ መደበኛ ጉባኤው የሚተላለፉ አቅጣጫዎችን በመከተል የክልሉ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮም ፌዴሬሽኑን ውጤታማ የሚያደርጉ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ኀላፊዋ አረጋግጠዋል።
በጉባኤው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ለፌዴሬሽኑ ሥራ መሳካት አስተዋጽኦ ለነበራቸው ተቋማት እና ግለሰቦች ምሥጋና እና ዕውቅና ተሰጥቷል።



