“ሀገር እና ሕዝብ ሰላም እንዲኾን በእናትነት ምክር፣ በሴትነት ብልሃት ከልብ መምከር ያስፈልጋል ” የአማራ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ትልቅሰው ይታያል/ዶር./

የአማራ ሴቶች ፌዴሬሽን 3ኛ መደበኛ ጉባኤውን በባሕር ዳር እያካሄደ ነው። ጉባኤው “የተደራጀ የሴቶች ተሳትፎ ለሰላም እና ለዴሞክራሲ” በሚል መሪ መልዕክት ከየካቲት 02/2017 ዓ.ም እስከ የካቲት 05/2017 ዓ.ም ነው የሚካሄደው።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ትልቅሰው ይታያል የሴቶችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ተሳታፊነት፣ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መነሻ የሚኾኑ ተግባራት ሲፈጸሙ ቆይተዋል ብለዋል።
ፌዴሬሽኑ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የአማራ ሴቶች ማኅበር፣ የነጋዴ ሴቶች፣ የሴት ደራሲያን፣ የአካል ጉዳተኛ ሴቶች፣ ትንሣኤ የቤት ሠራተኛ ሴቶች፣ ኑሮ በሀገሬ ከአረብ ተመላሽ ሴቶች እና አንጸባራቂ ወጣት ሴቶች ማኅበራትን አካትቶ የያዘ መኾኑን ጠቁመዋል። የአባላቱን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም በተደራጀ መንገድ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ፌዴሬሽኑ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሥራት ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ለ7 ሺህ 821 መሪዎች የአደረጃጀት እና የአመራር ክህሎት ሥልጠና ሰጥቷል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ ወደሁሉም የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች በማስፋት 517 ሴቶች በመጀመሪያ ዲግሪ እና በ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራም እንዲማሩ መደረጉንም ፕሬዝዳንቷ ገልጸዋል።
የአባል ማኅበራትን ዘላቂ የኢኮኖሚ አቅም የሚያጠናክር 5 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር መቀበላቸውንም ተናግረዋል። በቦታው ላይ የገበያ ማዕከል፣ የሙያ እና ክሕሎት ማሠልጠኛ፣ የሕጻናት ማቆያ፣ የእንግዳ ማረፊያ እንዲሁም የስፖርት ማዕከል ያካተተ ግንባታ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅቱ ተጠናቅቋል ብለዋል።
የሴቶችን የተደራጀ አቅም በመጠቀም ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የፍትሕ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች፣ የንብረት እና የመሬት ተጠቃሚነት ችግር እና ሌሎችንም በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን ለመከላከል ትግል ሲደረግ መቆየቱንም አንስተዋል።
የሁሉም ነገር መሠረት የኾነውን ሰላም በማስፈን ረገድም ሴቶች ያላቸውን ጥበብ በመጠቀም በልጆቻቸው እና በወንድሞቻቸው ፊት ዝቅ ብለው በመለመን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሊደርስ የነበረውን ግጭት ሙሉ በሙሉ አስቀርተዋል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ።
“የሴቶች መብት እና ደኅንነት እንዲጠበቅ ከተፈለገ ግጭት እና ጦርነትን በጋራ በመቆም በቃ ልንል ይገባል” ብለዋል።
ሁሉም ነገር ከሴቶች እና ከእናቶች ጥበብ እና ብልሃት በላይ አይደለም ያሉት ፕሬዝዳንቷ ሀገር እና ሕዝብ ሰላም እንዲኾን፣ የሴቶች መብት እና ደኅንነትም እንዲጠበቅ በእናትነት ምክር እና በሴትነት ብልሃት ከልብ መምከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ልዩነቶች በሰላም እንዲፈቱ የሚያስችሉ መድረኮችን በማመቻቸት እና የሚያቀራርቡ ምክረ ሀሳቦችን በመስጠት ለሀገር ሰላም መሥራት ይገባል ነው ያሉት። ችግር የሚፈጥሩ ወንጀለኞችን በማጋለጥ እና “ተው” በማለት በኩልም ሁሉም ሴቶች የሚያውቁበትን የእናትነት እና የእህትነት ጥበብ እና ብልሃት መጠቀም አለባቸው ብለዋል።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top