የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ “ጠንካራ የሴቶች የልማት ህብረት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተሣትፎና ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል ሞዴል የሴቶች የልማት ህብረቶችን ለመፍጠር ያለመ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ አካሂዷል።
በምክክር መድረኩ ላይ የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክቡር አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ክቡር አቶ ፍስሃ ደሳለኝ፣ የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይን ጨምሮ ሌሎች የቴክኒክ እና የስትሪንግ ኮሚቴ አመራሮች ተሳትፈውበታል።
ለውይይት መነሻ የሚሆን ጹሁፍ በቢሮው ምክትል ኃላፊ በወ/ሮ ዝና ጌታቸው አማካኝነት ቀርቦ ሠፊ ውይይት ተደርጎበታል ።
እስከታችኛው እርከን የሚገኙ ሴቶችን በሁሉም መስክ የሚኖራቸውን ትክክለኛ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ አደረጃጀቶች የሴቶች የልማት ህብረት አንዱና ዋነኛው ነው ያሉት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አደረጃጀቱን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።
ወይዘሮ ብርቱካን አያይዘውም እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ 367 ሞዴል የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀቶችን በቀበሌ ደረጃ ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በተለይ የዘንድሮውን አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በአደረጃጀቶች የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማጠናከር፣ የቁጠባና የብድር ስርዓትን ማጠናከር፣ የሴቶችን ማህበራዊ ተሣትፎ ማሳደግ እና የቦንድ ግዥ እንዲፈጽሙ ከጥምረቱ አባላትና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በላቀ ርብርብ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።
ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ከተናጠል ይልቅ በተደራጀ አግባብ ማሳተፍ እንደሚገባ ነው ኀላፊዋ የገለጹት፡፡
ሴቶች በልማት ህብረት ተደራጅተው በሁሉም መስኮች ለላቀ ተሣትፎና ተጠቃሚነት መብቃት እንዲችሉና የበለፀገ አስተሳሰብ ኑሯቸው በየአካባቢያቸዉ ችግሮቻቸዉን የሚፈቱበትን እድል ማስፋት እንደሚገባ ጨምረው አሳስበዋል።
የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊው ክቡር አቶ ፍስሃ ደሳለኝ በበኩላቸው ሴቶች ላይ መስራት አገር ላይ መስራት በመሆኑ ሁላችንም አደረጃጀቱን በመደገፍ ሆነ የሴቶችን ፋትሀዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን በልዩ ትኩረት ልንሰራ ይገባል። በተለይ አመራሩ ተግባራቶቹን በመፈፀም ግንባር ቀደም ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ክቡር አቶ ይርጋ ሲሳይ እንደተናገሩት፣ የአደረጃጀቶች ሁሉ አስኳል የሆኑትን የሴቶች የልማት ህብረት ጥምረቶችን ከንግግር ባለፈ በተግባር በማጠናከር እውነተኛ የሴቶችን ተሣትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀቶችን ማጠናከር የክልሉን እድገት ማፋጠን ነው ያሉት ኀላፊው ሴቶችን በጥምረቱ ማደራጀት፣ በተልዕኮ ማሰማራት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እና ሞዴል የሴቶች የልማት ህብረት አደረጃጀቶችን በቀበሌ ደረጃ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በህብረት ስራ ማህበራት፣ በስራና ስልጠና እንዲሁም በሌሎች መስኮች ያሉ እድሎችን በመለየት መጠቀም እና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
አደረጃጀቱን ጠንካራና ተናባቢ በማድረግ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱንና ተቀባይነቱን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባ የተናገሩት ክቡር አቶ ይርጋ በልማት ህብረቶች ሴቶችን ማሰባሰብ፣ ጥራትን ማሳደግ፣ ትስስርን መፍጠር፣ ለቀጣይ ስራዎች ማዘጋጀት እና ተልዕኮዎችን በውጤታማነት መፈፀምና ውጤታማነቱን መገምገም እንደሚገባ ጨምረው ተናግረዋል።


