ባሕር ዳር: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የሴት የሥራ መሪዎች ፎረም በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በፎረሙ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ተገኝተዋል።
ዶክተር ሙሉነሽ በፎረሙ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ‘ማርች 8’ የሚከበርበት ምክንያት የአውሮፓና አሜሪካ ሴቶች ለዓለም ሴቶች እኩልነት ያደረጉትን ትግል ለማስታወስ እና አረዓያነታቸውን በመከተል የአኹኑን ሴቶች መብት እና ጥቅም ለማስከበር መኾኑን ገልጸዋል።
በሁሉም ዘርፍ ሥራዎቻችንን እየገመገምን አጠናክረን በመቀጠል የሴቶችን ተጠቃሚነት የምናጠናክርበት ጊዜና ወቅት ላይ ነንም ብለዋል። ሴት መሪዎች ይህንን እድልም በአግባቡ በመጠቀም ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመተባበር እና በመደጋገፍ የተሠሩ እና የተገኙ ውጤቶችን እየገመገሙ የመሥራትን አስፈላጊነት አንስተዋል። የአመራርነት አረዓያነት ይጠበቅብናልም ብለዋል።
የሴቶች ድምጽ እና አቅም መኾን የምንችለው በሥራ እና በውጤት ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ጠንክረን በመሥራት ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል። ፎረሙንም እየተደጋገፉ ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሴቶችን የአመራር ተሳትፎ ማሳደግ፣ የፎረሙን እቅድ ክንውኖች በመገምገም ማጠናከር፣ በብሔራዊ የምክክር መድረኮች እና በሽግግር ፍትሕ ሂደት ሴቶች በንቃት በመሳተፍ አጀንዳቸውን ለማስያዝ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርስ ጥቃትን የመከላከል ሥራ አሁንም መረሳት የሌለበት መኾኑን አንስተዋል።


