ደሴ: የካቲት 30/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፍ የሴቶች በተለያዩ ሁነቶች ትናንት ተከብሯል።
ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ የዘንድሮው የሴቶች ቀን አከባበር ከአዳራሽ ውይይት ያለፈ እንደነበር አስታውቀዋል።
ቀኑ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወኑ የሚገኙ ሴቶችን የሥራ እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ እና ተሞክሮ በመውሰድ መከበሩንም አንስተዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ መሪዎች እስከ ቀበሌ በመውረድ በዓሉ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሚያሳይ መልኩ ተከብሯል ነው ያሉት፡፡
ከበዓሉ መከበር ሁለት ወራት አስቀድሞ በንቅናቄ ሴቶችን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እየተከናወኑ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ሴቶች በማድለብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በጓሮ አትክልት እና በሌሎችም የሌማት ትሩፋት የሥራ መስኮች በመሠማራት ውጤታማ መኾን እንደሚችሉ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተደረጉ የመስክ ምልከታዎች ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በተለይ ሴቶች ከአመጋገብ ሥርዓት መጓደል ጋር ተያይዞ የሚመጣውን መቀንጨር በመከላከሉ ሂደት ሚናቸው የጎላ በመኾኑ በሰፊው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ሢሠራ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡
በማኅበራዊ ተጠቃሚነት እናቶች በሕክምና እጦት እንዳይሞቱ እና ልጆቻቸው ሳይከተቡ እንዳይቀሩ ግንዛቤ የመፍጠር እና የማሕጸን በር ካንሰር ክትባት እንዲያገኙ ግብ ተቀምጦ ሲተገበር መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮው የሴቶች ቀን ከአዳራሽ ውይይት እና ቀኑን አስቦ ከመዋል ባለፈ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና ተሳታፊነት ባረጋገጠ መልኩ በልዩ ልዩ ሁነቶች በድምቀት መከበሩን ነው የተናገሩት።


