ባህርዳር፣ መጋቢት 10/2017ዓ.ም (አማራ ኮሙዩኒኬሽን) የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች አለማቀፍ የሴቶች ቀንን በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡
በዝግጅቱ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋየ የአማራ ክልል የህብሰተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሴቶችን ተሳትፎ በማጠናከር በሀገራችን ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሂደት ላይ የጎላ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው አስቦ የሴቶችን ቀን ማክበሩ ለሌሎች አርያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።
የብዓሉ መከበር ዋና አላማ የተገኙ ውጤቶችን ዕውቅና ለመስጠትና ያሉ ክፍተቶችን ለይቶ በመሙላት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጠናከር ነው ያሉት አፈ ጉባኤዋ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ ደግሞ ከታሠርንበት ልማድና አስተሳሰብ ልንወጣ ይገባል፡፡
በዚህም ሴቶች እኔ እችላለሁ፤ አካባቢየንና አገሬን እለውጣለሁ፤ የሚል እሳቤ በሴቶች ዘንድ መስረጽ እንዳለበት ተናግረዋል።
ሴቶች ድርና ማግ ሁነው ተሳስረው ከሰሩ የሀገርን ጥቅም ከማረጋገጥ አኳያ ድርሻቸው የጎላ ይሆናል። የዛሬው በዓል የሴቶችን ቀን ከመዘከር ባሻገር የየራሳችንን ድርሻ ወስደን መስራት እንድንችል ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ የገለጹት ወ/ሮ ፋንቱ ሴቶች ካሰቡት ደረጃ ለመድረስና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ራሳቸውን በትምህርት ማብቃት አለባቸው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሠላም ቢኖርም፣ ሴቶች ግንባር ቀደም በመሆን ስለ ” ሠላም ” መስበክ፣ የሀሳብ ልዩነቶችንም በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና የህግ የበላይነት እንዲከበር አስበው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ሴቶች ከልማት፣ ከዕድገት፣ ከሠላም፣ ከፈጠራ አኳያ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንስ፣ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በስነጹሁፍና በተለያዩ ጉዳዮች የኖቬል ተሸላሚ ናቸው። ይህም ሴቶች አቅም እንዳላቸው ያመላክታል ብለዋል።
ይሁን እንጂ ተሳትፎው በቁጥር ደረጃ ሲታይ ጥቂት ነው። ይህንን ተሳትፎ ወደ ሀምሳ በመቶ ከፍ ማድረግ ይገባል ያሉት ዳይሬክተሩ እውነተኛ ሠላም፣ ልማትና ብልጽግና እንዲመጣ ከተፈለገ ሴቶች ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው፤ ህብረተሰቡም ሊያበረታታና ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው ሴቶችን ያላሳተፈ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በግማሽ ጉልበት፣ ዕውቀት፣ ጥረት ላይ የሚመሠረት በመሆኑ የሚጠበቀውን ውጤት ማሳካት አይቻልም ብለዋል፡፡
ይህም ሴቶች የማህበረሰቡ የጀርባ አጥንት መሆናቸውንና ማናቸውም ልማት ያለሴቶች ውጤታማ እንደማይሆን አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
ወ/ሮ ብርቱካን አክለውም ጤና ለሴቶች ተደራሽ እንዲሆን የማህፀን ጫፍና የጡት ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ በቅንጅት እየተሠራ ሲሆን በተለይም ከኢንስቲትዩቱ ጋር የወባ ወረርሽኝንና ፆታዊ ጥቃትን ለመከላከልና በህብረተሰቡ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አዳጋዎችን ቀድሞ በመከላከል፣ ከተከሰቱም ቶሎ ምላሽ በመስጠት ረገድ አበረታች ስራዎች ተሠርተዋል ብለዋል።
በአለማቀፍ ደረጃ ለ114ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ49ኛ በክልል ደረጃ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል” በሚል መሪ ሀሳብ ተክብሯል።


