በጎንደር ቀጠና የሚገኙ የአራት ዞኖችና የጎንደር ከተማ አሰተዳደር የሃይማኖት አባቶችና የሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ዘርፍ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የውይይት መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ እደገለፁት በክልሉ ጎጅ ባህላዊ ድርጊቶችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት አባቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው ።
በክልላችን በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክኒያት የሚፈፀሙ የጎጅ ባህላዊ ድርጊቶች መጠን እየጨመረ መሄዱን የገለፁት ቢሮ ኃላፊዋ በተለይ ሴቶች የጎጅ ባህላዊ ድርጊቶች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሴቶች ጥቃት ሲደርስባቸው የፍትህ አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል ያሉት ወይዘሮ ብርቱካን በፍትህ ማሻሻያ ፕሮግራም ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የጤና ተቋማትም በአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ከጤና ተቋማትና ከሆስፒታሎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች የጎጅ ባህላዊ ድርጊቶች ፈፃሚና አስፈፃሚ መሆን የለባቸውም ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ የሃይማኖት አባቶች ሃላፊነታቸውን በተገቢው መንገድ መወጣት እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በእለቱ ለውይይቱ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ደግሞ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ጎጅ ባህላዊ ድርጊቶች የሚያስከትሉት ጉዳት እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም አሁንም ብዙ ስራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
ጎንደር በርካታ የሃይማኖት አባቶችን ያፈራ ከተማ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የሃይማኖት ተቋማት ጎጅ ባህላዊ ድርጊቶችን በመከላከል ያለባቸውን ሃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩን ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስልጣናት አባ ዮሴፍ ደስታ ደግሞ ያለ ዕድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን የሚያበረታታ ሃይማኖታዊ ስርዓት የለም፡፡
ሁላችን የሃይማኖት አባቶች የጎጅ ባህላዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በውይይ ላይ የተነሱ ሃሳቦች መድረኩን በመሩት የሃይማኖት ተቋማትን ወክለው በተገኙ የሃይማኖት አባቶችና የአማራ ክልል ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ ምላሽ ተሰጥቶ ውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡


