ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ለአስከፊ ድህነት ሊዳረጉ ይችላሉ:: መሰረታዊ አጋላጭ ምክንያቶች የሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሲሆኑ የአካባቢ መራቆትና የሚያስከትለው የምግብ ዋስትናን የማጣት ችግር፣ የአየር ንብረት መዛባትና እሱን ተከትሎ የሚመጣ ድርቅና የኢኮኖሚ መዛባት ችግር፣ ጦርነትና ግጭቶች የሚያስከትሉት የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መናጋት ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዙሪያ በሚፈጠር የፍትሃዊነት መጓደል ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠር ዝቅተኛ የሥራ ባህል ፣ የሥራ አጥነት ችግር፣ በእድሜ መግፋት፣ በጤና ችግር አቅማቸው ሲዳከም፣ በአካል ጉዳት ምክንያት የተሳትፎ እድላቸው ሲጠብና የመስራት ችሎታቸው ሲቀንስ፣ ወ.ዘ.ተ. በአጠቃላይ ዜጎች በምርትና የገበያ ውድድር ስርዓቱ ያላቸው ተሳትፎ እየጠበበና እየተገለሉ ሲመጡ ለድህነትና ከዚያም ለአስከፊ ድህነት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ተጋላጮች አስተማማኝ የማህበራዊ ድጋፍ ካልተደረገላቸው በተለያዩ የአስከፊ ድህነት መገለጫ ለሆኑ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ በተለይም መጠለያ አልባ የመሆንና መደበኛ ባልሆን መጠለያ የመኖር፣ ከመኖሪያ አካባቢ የመፍለስና በጊዚያዊ መጠለያ የመጠለል፣ ለሴተኛ አዳሪነት የመዳረግ፣ ወደ ጎዳና የመውጣት፣ ወደ ልመና ውስጥ የመግባት ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡
ዜጎችን ከአስከፊ ድህነት ለመታደግና እሱን ተከትሎ ከሚመጣ ችግር ለመከላከል የተለያዩ የማህበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ሊተገበሩ ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር በብሄራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መተግበር አንድ እርምጃ ወደፊት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የፖሊሲው የትግበራ ሂደት ከሞላ ጎደል የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ተጀምሯል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
የአብክመ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከጠቅላላ የክልላችን ህዝብ 70 ፐርሰንት እና በላይ የሚሆኑ እና በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተለየ ድጋፍ እና እንክብካቤ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ አረጋዊያንንና አካል ጉዳተኞችን እንዲሁም ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎች፣ ለምኖ አዳሪዎች ፣ ሴተኛ አዳሪዎች መብትና ደህንነት እንዲጠበቅ ፣ በሁሉም መስክ የሚኖራቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲያድግ ፣የወጡ የህግ ማእቀፎች፣ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚሰራ ተቋም ነው፡፡
በመሆኑም ተቋሙ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት ለመወጣት ከሚተገብራቸው ተግባራት መካከል የወጡ የህግ ማቀፎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መስራት ተጠቃሾች በመሆናቸው ለዞን እና ወረዳ ለተውጠጡ የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያና መከታተያ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች የአዕምሮ ጤና ፣ ስነልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ከመጋቢት 26/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በባህርዳር ከተማ በባህር ዳር ከተማ እየሰጠ ይገኛል፡፡
የስልጠና መድረኩን በንግግር የቢሮው የማህበራዊ ጥበቃ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በላነው ጸጋ ተቋሙ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ሲከሰቱ ይበልጥ ተጠቂዎችና ተጋላጭ ሰፊ የህብረተሰብ ክፍሎችን ይዞ በሁሉም መስክ የሚኖራቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ መብትና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚሰራ ተቋም እንደሆነ ጠቁመው ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር በባለሙያዎችም ሆነ በሌሎች የሚደርሱ አዕምሯዊ፣ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ ጫናዎች በማስወገድ ሌሎች ላይም መነቃቃት በመፍጠር በቀሪ ጊዚያት ለተቋሙ ደንበኞች የተሸለ ጠጠቃሚነት እንዲሰሩ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚሰጥ ሲሆን የአዕምሮ ጤና ፣ ስነልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ፣የጉዳይ አያያዝና በማህበረሰብ ድጋፍና ክብካቤ ጥምረት አሰራርና አደረጃጀት ማንዋል ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡


