.“ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠር የበጎነት ተግባር ብቻ ሳይኾን ኀላፊነታችንም ነው” የጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ በኢትዮጵያ ለ31ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለምአቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በተለያዩ ልማታዊ የድጋፍ ሥራዎች አከበረ፡፡
በበዓሉ ማጠናቀቂያ ሥነ ሥርዓት መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፍሬሠላም ዘገየ ”ስለአካል ጉዳተኞች በአዳራሽ ውስጥ መነጋገር ብቻ ሳይኾን ከአዳራሽ ውጪ ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት ይገባል” ብለዋል።
በአማራ ክልል 20 ሚሊየን አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ፍሬሠላም ”አካል ጉዳተኞች ተሳታፊና ተጠቃሚ የምንኾንበት ሥርዓት ለመፍጠር ተቋማዊ ምላሽና ውክልና ያስፈልገናል” በማለት እንደሚያስፈልግ አጽዕኖት ሰጥተው አሳስበዋል።
የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኀላፊ ንጹህ ሽፈራው የአካል ጉዳተኞችን ቀን ስናከብር መንግሥታዊ ተቋማት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በፕሮግራሞቻቸው አካተው ጭምር መኾን እንዳለበት አሳስበዋል። ቢሯቸው ግንዛቤ በመፍጠር፣ የአካል ተሐድሶ ተቋማትን በማጠናከርና የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በመከታተልም እየሠራ መኾኑንም ወይዘሮ ንጹህ ሽፈራው ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ባለፉት አራት ዓመታት በኮቪድና የሰሜኑ ጦርነት ለአካል ጉዳተኞች የከፋ ችግር ጊዜ እንደነበር ጠቅሰው መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ችግር ለማቃለል የእቅዱ አካል አድርጎ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
”ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠር የበጎነት ተግባር ብቻ ሳይኾን ኀላፊነታችንም ነው” ያሉት አቶ አብዱልከሪም የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማሳደግ የአንድ ተቋም ዕዳ ብቻ ሳይኾን የሁሉም ኀላፊነት መኾኑን ገልጸዋል። ስለኾነም ስለ አካል ጉዳት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማስተካከል በየደረጃው የሚገኝ አመራር፣ ባለሙያና ኅብረተሰቡ በመደጋገፍ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አቶ አብዱልከሪም አሳስበዋል።
በማጠናቀቂያ ሥነ ሥርዓቱ የክልል የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ አካል ጉዳተኞችና አረጋውያን እንዲሁም ሲቪል ማኅበራት ተገኝተዋል።
ለ5 በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ ለሆኑ ሞዴል አካል ጉዳተኞች ፥ ለ63 አቅመ ደካማ አካል ጉዳተኞችና በግጥምና ስነፁሁፍ ውድድር አሸናፊ ለሆኑ ሁለት አካል ጉዳተኞች ለእያንዳንዳቸው ከ3 ሺህ እስከ 10ሺህ ባጠቃላይ ከ2 መቶ 40 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል። በተቋማቸው የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ አካቶ በመተግበርና ምቹ የስራ ከባቢ ለፈጠሩና አስፈላጊ ግብአት ላሟሉ መንግስታዊ ተቋማት እና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተቋሙ ጋር በትብብር እየሰሩ ላሉ ድርጅቶችም የእውቅናና የምስጋና ሰርትፍኬት ተበርክቶላቸዋል።